ማህበረሰቡ እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ የአካል ብቃቱን የሚያዳብርባቸው፣ የተዳከመ አዕምሮውን የሚያፍታታባቸው፣ የዛለ አካሉን የሚያነቃቃባቸው፣ በትርፍ ጊዜው እና በበዓላት ቀን ማኅበራዊ ግንኙነቱን የሚያጠናክርባቸው ሀገር በቀል እውቀቶች ውጤት የሆኑ የባህል ስፖርቶች አሉት። እንደ ገና፣ የጥምቀትና መሰል በዓላት ደግሞ ከኃይማኖታዊ ይዘታቸው ባሻገር የማህበራዊ ትስስር መገለጫ የሆኑት ባህላዊ ስፖርታዊ ሁነቶች ጎላ ብለው የሚታዩባቸው ናቸው።
የባህል ስፖርቶችና ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተዋወቁ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይም የገና ጨዋታ እና የፈረስ ጉግስ በከተማዋ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። ሆኖም ስፖርቶቹ በየዓመቱ በወጥነት ይካሄዳሉ ወይ? ባህላዊ ስፖርቶቹን ዘወትራዊ ለማድረግ ምን አይነት ስራዎች ሊሰሩ ይገባል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች በስፖርት ቤተሰቡ የሚነሱ ናቸው።
በዘመናዊው የፈረስ ጉግስ ላይ አተኩሮ የሚሰራው የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት ማህበር ፅህፈት ቤት ኃለፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ ከዚህ ቀደም ለዝግጅ ክፍላችን በሰጡት አስተያየት ባህላዊ ስፖርቶች እንደ ዕድሜያቸው ማደግ ያልቻሉበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡ በቂ ውድድሮች ያለመኖር፣ የባለሙያ እጥረት መኖርና አዳጊዎች በትምህርት ቤቶች ስለስፖርቱ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያለመደረጉ ባህላዊ ስፖርቱ እየተጋፈጣቸው ያሉ ዋና ዋና ችግሮች ስለመሆናቸው ይገለጻል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መረጃ መሰረት በአሁኑ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ ባህላዊ ስፖርቶችን ከወቅታዊ ዝግጅት ባለፈ በቋሚ መዋቅር ለመምራት የሚያስችሉ ተግባራትን እየከወነ ይገኛል። በከተማ አስተዳደሩ በኩል ይህን ባህላዊ ስፖርቶችን ለማነቃቃት በየዓመቱ የገና ጨዋታ ውድድሮችን የማዘጋጀት ልምድ እየዳበረ መጥቷል። እንደ ጃንሜዳ ባሉ ትልልቅ ክፍት ቦታዎች ባህላዊ የገና ጨዋታ በደመቀ ሁኔታ እንዲካሄድ ድጋፍ ይደረጋል። የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚሳተፉባቸው መሰል ውድድሮችም ይካሄዳሉ።
የባህል ስፖርቶች በዘፈቀደ ከመካሄድ ይልቅ በወጥነት እንዲመሩ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ውድድሮቹ በህግና በደንብ እንዲመሩ፣ የዳኝነት ስልጠናዎች እንዲሰጡ እየተደረገ ነው። የባህል ስፖርቶች በየዓመቱ በተወሰነ ጊዜና ቦታ እንዲካሄዱ በማድረግ ህዝቡ አስቀድሞ እንዲያውቃቸው የማድረግ ስራዎች ተጀምረዋል።
የባህል ስፖርቶች በወጥነት እንዲካሄዱ ለማድረግ ትልቁ እርምጃ የተወሰደው በስፖርት ማህበራት አደረጃጀት ላይ ነው። የአዲስ አበባ ባህላዊ ስፖርት ፌዴሬሽን አሁን ላይ በየክፍለ ከተማው ያሉ ክለቦችን በማደራጀት የገና ጨዋታ በውድድር መልክ እንዲካሄድ እያደረገ ነው። ይህ ቀደም ሲል በየሰፈሩ ይደረግ ከነበረው ይዘት ወጥቶ በዳኝነትና በደንብ እንዲመራ አድርጎታል። የከተማዋ ስፖርት ኮሚሽን በየዓመቱ ለበዓል ስፖርቶች የሚሆን በጀት በመመደብ፣ አሸናፊዎች የሚሸለሙበትና የሚበረታቱበትን ሥርዓት ስለመዘርጋቱ የፌዴሬሽኑ መረጃ ያሳያል።
አሁን ላይ እየተካሄደ ያለው 16ኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫልም ስፖርቱን በማሳደግ ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ ‘የባህል ስፖርቶች ተደራሽነት ለሀገር ማንሰራራት’ በሚል መሪ ቃል በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አስተናጋጅነት መካሄድ ጀምሯል። በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መገለጫ የሆኑት የባህል ስፖርቶች አብሮነትን፣ ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን ለማጠናከርና ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት ሚናቸው የጎላ በመሆኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የባህል ስፖርቶች ለዘመናዊ ስፖርት መነሻ ናቸው ያሉት አቶ በላይ በከተማ አስተዳደሩ በትምህርት ቤቶች የአዳጊ ወጣቶች የባህል ስፖርት የስልጠና ፕሮጀክቶች በመክፈት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የውድድሩ ዋና ዓላማም የከተማ አስተዳደሩን ወክለው በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር የሚሳተፉ ውጤታማ ስፖርተኞችን መምረጥ እንደሆነ የቢሮ ኃላፊው አሳውቀዋል።
በ12 የስፓርት አይነት በሚካሄደው ውድድር አስራ አንዱም ክፍለ ከተማ እንደሚሳተፉ የገለጹት የስፖርት ማህበራት ውድድር ማደራጃ ዳይሬክተሩ አቶ አያሌው ታደለ ምርጥ ስፖርተኞ ሐረሪ ብሔራዊ ክልል በሚያዘጋጀው ሀገር አቀፍ ውድድርና ፌስቲቫል የከተማ አስተዳደሩን ወክለው እንደሚሳተፉ አሳውቀዋል፡፡
በ16ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ላይ ከአስር ሺህ በላይ የስፓርት ልዑካን ይሳተፋሉ፤ ውድድሩ ከታህሳስ 18 እስከ 26 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃደ ጫካ ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት ባሕላዊ ስፖርቶች ለዘመናዊ ስፖርቶች መነሻ በመሆናቸው ታሪካዊ እሴቶቻቸውን በመጠበቅና በማስፋፋት ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ ቢሆንም በቂ አይደለም ይላሉ፡፡ የባህል ስፖርቶች ለዘመናዊ ስፖርት መነሻ ቢሆንም እንዲያድጉና ዓለም አቀፍ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር ቀሪ የቤት ስራ መኖሩንም ገልጸዋል።
ስፖርቶች እንዲያድጉ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ታሪካዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲተላለፋና ስፖርቱ ይበልጥ እንዲዘወተር ውድድሮችን መጨመር፣ የባህላዊ ስፖርቶች ጠንካራ የስፖንሰር መሰረት እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ እስካሁን የተሰራውም ስራ በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ በትኩረት ይሰራባቸዋል ያሏቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በአጠቃላይ በባህል ስፖርቱ ላይ ተማሪዎች እንዲሳተፉ በማድረግ ውድድሮች እንዳይቋረጡ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ የባህላዊ ስፖርት በትኩረት ተሠርቶበት አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ መሆን ይገባዋል የሚለውም ሌላኛው አስተያየታቸው ነው፡፡
በተለይ እንደ የፈረስ ስፖርት ያሉ ባህላዊ ስፖርቶች በተለያዩ ሀገራት በመዝናኛነት፣ ገቢ ማስገኛ እና የሚጎበኝ የቱሪዝም ዘርፍ እስከመሆን ደርሷል። በዓለም እንደሚዘወተረው ዘመናዊ አሠራርን የተከተለ ያልሆነውን የፈረስ ስፖርት ወደ ነበረበት ዝናው ለመመለስ የውድድር ዕድሎችን ማመቻቸት፣ ከዓለም አቀፍ የፈረስ ስፖርት ማህበራት ጋር ግንኙነት ማጠናከር፣ የባለሙያዎችን ቁጥር ለመጨመር ስልጠናዎችን በማዘጋጀት አስታዋሽ የሚፈልግ ስፖርት ነው፡፡
በእርግጥ በአዲስ አበባ ከተማ የባህል ስፖርቶችን በወጥነት ለማካሄድ የተጀመሩት ተቋማዊ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው። ሆኖም ስፖርቶቹ ከባህል ትርዒትነት ባለፈ ራሳቸውን የቻሉ የኢኮኖሚና የቱሪዝም ዘርፍ እንዲሆኑ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት የግድ ይላል የሚሉት ደግሞ የባህላዊ ስፖርቶችን በዳኝነት የሚመሩት አቶ ይልቃል ደምሴ ናቸው። የአዲስ አበባን የበዓል ስፖርቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚከተሉት ነጥቦች በትኩረት ሊሰሩባቸው ይገባልም ይላሉ፡፡
የገና ጨዋታን እንደ ‘የኢትዮጵያ ሆኪ’ ለዓለም በማስተዋወቅ የውጭ ቱሪስቶች በበዓል ወቅት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ማድረግ። በየክፍለ ከተማው ያሉ የባህላዊ ስፖርት ክለቦች ቋሚ ማዘውተሪያና የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው ድጋፍ ማድረግ። የውድድሮችን ውጤትና ታሪክ በገፀ ድሮችና በማህበራዊ ሚዲያ በማስተዋወቅ ወጣቱ ስፖርቱን እንዲለምደው ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያው ይመክራሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብ የበዓል ስፖርቶችን ወደ ‘ከተማዊ ፌስቲቫል’ ማሳደግ ነው። ስፖርታዊ ውድድሮቹ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ የገና ጨዋታን እና ሌሎች ባህላዊ ስፖርቶችን በዩኔስኮ (UNESCO) ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይገባል።
የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በገና ወቅት አዲስ አበባ መጥተው እነዚህን ውድድሮች እንዲመለከቱ በማድረግ የከተማዋን ገቢ ማሳደግ በሁሉም ሰፈሮችና ትምህርት ቤቶች የበዓል ስፖርቶች የውድድር አካል እንዲሆኑ ማድረግ በቀጣይ በትኩረት ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን የባህል ስፖርቶች እንዲጎለብቱ ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና ፌሰቲቫል እንድታዘጋጅ መመረጧ ይታወሳል።
በሳህሉ ብርሃኑ