ለገና በዓል የሚውሉ የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች፣ እንዲሁም የእርድ እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽዖዎች በበቂ ሁኔታ ለገበያ መቅረባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽነር ወይዘሮ ሽታዬ መሐመድ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ በበዓሉ ወቅት የፍጆታ ምርቶች እጥረት እንዳይከሰት ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። በመሆኑም ኅብረተሰቡ ያለምንም ስጋትና መሽቀዳደም የገበያ ግብይቱን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጽም ጥሪ አቅርበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ለሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት 325 ቢሊዮን ብር በመመደብ፣ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ እንዲቀርቡ ማድረጉን ገልጸዋል። በዚህም መሠረት
የጤፍ፣ የዱቄትና የምግብ ዘይት አቅርቦት በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።
ዶሮ፣ እንቁላልና የእርድ በሬዎች በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ለገበያ ቀርበዋል። ከኦሮሚያ ክልል ሎሜ፣ አዳማ እና ሞጆ አካባቢዎች የእርድ በሬዎች ወደ መዲናዋ እየገቡ መሆኑ ተረጋግጧል።
በከተማዋ በሚገኙ 267 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሉካንዳ ቤቶች አማካኝነት ሥጋ በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውም ተገልጿል።
በዓሉን ተገን በማድረግ የሚፈጠር አላስፈላጊ የዋጋ ንረትና የንግድ አሻጥርን ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የገለጹት ኮሚሽነሯ ተገልጿል በምክትል ከንቲባ የሚመራና ከንግድ ቢሮ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተውጣጣ የተቀናጀ ግብረ ኃይል ወደ ሥራ መግባቱም ተናግረዋል።
ግብረ ኃይሉ በየደረጃው ከሚገኙ የቁጥጥር አካላት ጋር በመቀናጀት የገበያውን መረጋጋት የማረጋገጥና ሕገ-ወጥ አሠራሮችን የመከላከል ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑን ኮሚሽነሯ ዛሬ በሰጡት መግለጫቸው አብራርተዋል።
በምትኩ ተሾመ