የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ለአገልግሎት ክፍት ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የንባብ ባህል እንዲዳብር፣የዕውቀት ልውውጦች እንዲኖሩ እና ከዓለም ጋር በዕውቀት መገናኘት እንዲቻል ድልድይ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
አብርሆት ቤተ ጻህፍት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እንዲሁም የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ ታህሣሥ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ተመርቆ ለአገልሎት ክፍት ከሆነ በኋላ፣ ላለፉት አራት ዓመታት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች ዓመቱን ሙሉ የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
በዚሁ ወቅት መልዕክ ያስተላፉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአብርሆት ቤተ መጻህፍት ለአገልግሎት ክፍት ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ የንባብ ባህል እንዲዳብር፣ የእውቀት ልውውጦች እንዲኖሩ እና ከዓለም ጋራ በእውቀት መገናኘት እንዲቻል ድልድይ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱን ጠቁመው በቀጣዮቹ ዓመታት አገልግሎቱን በማላቅ ከፍ ባለ ደረጃ ለማገልገል እራሱን በማዘመን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
በቤተ መጻሕፍቱ ይፋ የተደረጉት ሲስተሞች የተቀናጀ ቤተ መጻህፍት አስተዳደር ስረዓት፣ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት እና የምርምር መድረክ መሆናቸውንም ገልጸዋ፡፡
ከንቲባ አዳነች አክለውም፣ ሲስተሞቹ ምቹ የጥናት እና ምርምር ሁኔታን የሚፈጥሩ እና ታሪካዊ ብሎም ሳይንሳዊ ጥናቶችን በዲጂታል ጥበቃ ደረጃ ከፍ በማድረግ የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም እውቀት ለሀገር ግንባታ መዋል እንዲችል እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትስስርን ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፣ ዜጎች በተመቻቸው እድል በመጠቀም የእውቀት አድማሳቸውን እዲያሳድጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሲስተሙን በማበልጸግ ሂደት እና አገልግለት ላይ እንዲውል በማድረግ ሂደት አስተዋፅዖ ላደረጉ አካላትም ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የአብርሆት ቤተ መጻህፍት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ታሪኩ፣ ቤተ መጻህፍቱ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተሞክሮዎችን በመውስድ እና አሰራን በማዘመን ለዜጎች እና ነዋሪነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የውጭ ሀገር ዜጎች የሚመጥን አገልግሎት የመስጠት ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የአብርሆት ቤተመጻህፍት በዓመት እስከ 1.8 ሚሊየን ተጠቃሚዎች ያሉት መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በሀብታሙ ሙለታ