የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሰፈሩት ዛሬ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሂዷል።
በዛሬው ውይይት ላይ የተሳተፉት ተቋማት በለውጥ አስተሳሰብ የተካተቱና የተለያዩ የማኀበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉም የተካተቱበት በመሆኑ፣ በጋራ ከምናከናውናቸው ስራዎች በተጨማሪ በየተቋሞቻቸው ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት በምናደርገው ርብርብ የማይተካ ሚና አላቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
አዲሱ ምክር ቤት በአዲሱ ፖሊሲ፣ አዋጅ እና የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ላይ በመመስረት፤ የሕዝብን አቅም በማስተባበር የማይበገር ማህበረሰብ ለመገንባትና የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ጉዳት በቀነሰ መልኩ ለመከላከል በትጋት ይሠራል ብለዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት ስርዓታዊና ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባም በስብሰባችን የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል።
ከ2016 ክረምት ጀምሮ በተቀረጹ ፍኖተ-ካርታዎች መሠረት ልመናና ተረጂነትን በምርታማነት ለመተካት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ፤ ውጤትም እየተመዘገበ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
በዘላቂነት አስተማማኝ የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ መገንባት፣ የመጠባበቂያ ክምችትን በፌደራልና በክልሎች ማደራጀትና ተፈናቃይ ዜጎቻችን በዘላቂነት ተቋቁመው ወደ አምራችነት እንዲመለሱ ማድረግ የመንግሥታችን ዋነኛ ግብ ነው።
በተለይም የማኀበረሰባችንን የመደጋገፍ መልካም ልምምድ እና የአጋርነት እሴት በማጎልበት በየአካባቢያችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የምናደርገው ርብርብ ሰፊ ትኩረት የሚሰጠው እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት ጉዟችን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በዕውቀትና በጥበብ መሻገርን ይጠይቃል።
ይህንንም በመደመር ዕይታና በጠንካራ አመራር ለማሳካት ከስምምነት ላይ ደርሰናል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንደ ሀገር መላውን ማህበረሰብ ማንቀሳቀስ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል ገልጸዋል፡፡የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንደ ሀገር መላውን ማህበረሰብ ማንቀሳቀስ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።