የሚጥል በሽታ (Epilepsy) በጭንቅላት ውስጥ ባሉ የነርቭ ሴሎች መዛባት ምክንያት የሚከሰት ሲሆን፣ በየትኛውም ዕድሜ የሚገኝ ሰውን ሊያጠቃ የሚችል ከባድ የጤና እክል ነው።
በሽታው ተላላፊ ባይሆንም ተገቢው ሕክምናና ጥንቃቄ ካልተደረገለት ለከፋ አደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል በራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል የሥነ አዕምሮ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ዘመኑ ሀሰን ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል።
የሚጥል በሽታ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ቢችልም፣ በዋናነት በወሊድ ወቅት በሚደርስ የጭንቅላት መጎዳት፣ በአደጋ በሚደርስ የራስ ቅል ጉዳት፣ በማጅራት ገትር በሽታ፣ በጭንቅላት ኢንፌክሽን እና በጭንቅላት ዕጢ ሕመም መጠቃት አንዳንድ ጊዜም በዘር እንደሚተላለፍ ዶ/ር ዘመኑ አብራርተዋል።

እንደ በሽታው ደረጃ ዓይነት ምልክቶቹ ሊለያዩ ቢችሉም፣
፨ በድንገት መውደቅ
፨ ከአፍ አረፋ መውጣት
፨ ምላስ መንከሰ
፨ ለጥቂት ሰከንዶች የሚቆይ መፍዘዝ
፨ ሰውነትን መቆጣጠር አለመቻል
፨ የሽንት ማምለጥ
የበሽታው ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው።
የሚጥል በሽታ ሙሉ በሙሉ የሚድን ባይሆንም፣ በዘመናዊ ሕክምናና በሀኪም በሚታዘዙ መድኃኒቶች መቆጣጠር ይቻላል።
መድኃኒቶቹን በትክክልና ያለማቋረጥ በመውሰድ ታካሚው መደበኛ ሕይወት እንዲመራ ይረዳዋል።

የበሽታው ተጠቂዎች እሳት አጠገብ፣ ውሃ (ዋና) እና ከፍታ ቦታዎች ላይ ብቻቸውን መሆን የለባቸውም፤ በሚወድቁበት ጊዜ የከፋ አካላዊ ጉዳት እንዳይደርስ ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ነው ባለሙያው ያብራሩት።
በቂ እንቅልፍ ማግኘት፣ ከፍተኛ ጭንቀትንና ድካምን መቀነስ እንዲሁም መድኃኒትን በራስ ፈቃድ አለማቋረጥ በሽታውን ለመቆጣጠር ይረዳል።
በሚጥልበት ጊዜ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎችን በተመለከተም ዶ/ር ዘመኑ ሲያብራሩ ፥

፨ ከጠንካራ ነገሮች ማራቅ
፨ ከጭንቅላት ስር ለስላሳ ነገር (ትራስ ወይም ጨርቅ) ማድረግ
፨ በጎኑ ማስተኛት ተመራጭ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በሚጥልበት ጊዜ አፉ ውስጥ ማንኪያ ወይም ጨርቅ መክተት እና አፍን መያዝ የተሳሳተ በመሆኑ ከእንዲህ አይነት ድርጊቶች መቆጠብ እንደሚገባ ዶ/ር ዘመኑ ሀሰን አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸዉ