የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የግብር ስወራን ለመከላከልና የንግድ ሥርዓቱን ፍትሀዊነት ለማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተሰራ የተቀናጀና ድንገተኛ ኦፕሬሽን፣ ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ 6 ድርጅቶችንና 9 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ።
ቢሮው በዛሬው ዕለት መርካቶን ጨምሮ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች በሚሸጡ የንግድ ድርጅቶች ላይ ባካሄደው የኦፕሬሽን ተግባር 6 ድርጅቶች በሕግ የተጣለባቸውን የደረሰኝ አጠቃቀም ግዴታ ባለመወጣት ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በላከው መረጃ ገልጿል።

በዚህም ከድርጊቱ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው 9 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የመንግስትን ግብር ለመሰወር ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተገኝተው በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውን አሳውቋል፡፡
የኦፕሬሽን ተግባሩ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ማካሄዱን የገለጸው ቢሮው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የመንግሰትን ጥቅም ለማሳጣት ከግብር ህግ ጋር በተፃረረ መልኩ ያለደረሰኝ ሽያጭ በመፈፀም ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፖሊስ ተይዞ ለፍርድ የሚቀርቡ ይሆናል ብሏል፡፡
በቀጣይ ቀናትም ቢሮው የኦፕሬሽን ተግባሩን በሌሎችም ዘርፎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቶችን በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅም ህብረተሰቡም በ7075 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም መሰል ወንጀሎችን እንዲያጋልጥ ተጠይቋል፡፡
ቢሮው ከአስራ አምስት ቀናት በፊት በጎማ ነጋዴዎች ላይ ባካሄደው ተመሳሳይ የኦፕሬሽን ተግባር በ11 የንግድ ድርጅቶች ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ በተገኙ 15 ነጋዴዎች በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉ አይዘነጋም፡፡