ሴና ፋሽን ያዘጋጀው የ120 የሀገር ባህል አልባሳት የቀረቡበት የፋሽን ትርዒት በአዲስ ኢንተርናሽናል ማዕከል ተካሂዷል።
ትውልዱ በሀገር ባህል አልባሳት የሚኮራና የሚዋብ እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎችን ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ባሕል ኪነ ጥበብ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሉባባ ጀማል በመድረኩ ተናግረዋል።
በዘመናዊነት ስም ማንነታችንን እንዳናጣ ይህን መሰል ትርኢቶች አስፈላጊ ናቸው ሲሉም ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ገልፀዋል።
መንግስት ኢትዮጵያ ታምርት በመሳሰሉ “ኢኒሼቲቮች” የሀገር በቀል ምርቶችን እያበረታታ እንደሚገኝ የጠቀሱት ሉባባ ጀማል በባህልና በእደጥበብ ዘርፎችም ልዩ ትኩረት በማግኘቱ የቱሪዝም ዘርፉን እያሳደገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የባህል ማንነትን የሚያጠናክሩ ብሄራዊ ኩራትን የሚያላብሱ መሰል የፋሽን ትርኢቶች በከተማዋ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል።
የ”ከንሴና” 2026 የፋሽን ትርኢት አዘጋጅ ሴና ግርማ ውድድሩ የተሰናዳው የሀገር ባህል አልባሳትን በማስተዋወቅ ዜጎች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው በአልባሳቱ እንዲዋቡ ለማስቻል ለማስቻል ነው ስትል ገልፃለች።
በዘርፉም አዳዲስ ሞዴሎችንና ዲዛይነሮችን በማበረታታት አማራጭ የስራ እድሎችን ማስፋት እንደሚያስችል ሴና ግርማ ተናግራለች።
የትርዒቱ ተሳታፊ ሞዴሎች መሰል መድረኮች መዘጋጀታቸው ወደፊት ለሚያስቧቸው አለምአቀፋዊ ውድድሮች ጭምር ልምድ የሚያገኙበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በታምሩ ደምሴ