እኤአ 1970ዎቹ እንደ ሊድስ ዩናይትድ እና ማንችስተር ዩናይትድ ውጥረት የበዛበት ጨዋታ ማግኘት ከባድ ነው።
የሊድስ ዩናይትድ ደጋፊዎች ’’ሊድስ ዩናይትድ ሰርቪስ ክሪው’’ ፤ የማንችስተር ዩናይትዶቹ ደግሞ ’’ሬድ አርሚ’’ የሚል ቅፅል ስም በመያዝ ግጥሚያው በመጣ ቁጥር የአካል ጉዳት ያደረሰ ድብድብ ተለመደ ነበር፡፡
ሊድስ ዩናይትድ በዮርክሻየር ፣ ማንችስተር ዩናይትድ ደግሞ በላንክሻየር ግዛት ውስጥ ያሉ ግዙፍ ከተሞች ናቸው፡፡ በእንግሊዝ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች 64 ኪሎ ሜትር ብቻ ይለያቸዋል፡፡
በዚህ ቅርበታቸው መነሻ ከመጀመሪያው ግንኙነታቸው እኤአ 1923 ጀምሮ ባላንጣነታቸው እያደገ መጥቷል፡፡ ዩናይትድ ኤሪክ ካንቶና እና ሪዮ ፈርንዲናንድን የመሰሉ ኮከቦችን ከሊድስ ማስፈረሙ የፉክክር ደረጃቸውን ይበልጥ ከፍ አድርጎት ነበር።
በእርግጥ የሊድስ ዩናይትድ መዳከም ፤ የዩናይትድ ደግሞ የሀገሪቱ ሃያል ክለብ መሆን የደረጃ ልዩነቱ እንዲሰፋ አድርጎታል፡፡
በተለይ ሊድስ እኤአ 2004 ወደ ታችኛው ዲቪዚየን ሲወርድ የሁለቱ ክለቦች ተቀናቃኝነት ተቀዛቅዟል፡፡ ሊድስ አሁንም እራሱን በፕሪምየር ሊጉ አደላድሎ ለማስቀመጥ እየታገለ ይገኛል፡፡ ማንችስተር ዩናይትድም የቀድሞ ግርማ ሞገሱ ላይ አይገኝም፡፡
ሁለቱ ክለቦች በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም ግን ጨዋታቸው ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ዛሬ ቀን 9፡30 በኤላንድ ሮድ የሚያደርጉት ፍልሚያም ከዚህ አይለይም፡፡
ሊድስ ዩናይትድ ሰሞነኛ ብቃቱ ጥሩ ነው፡፡ ለመሰናበት ተቃርበው የነበሩት ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዳንኤል ፋርከ አሁን ነብስ ዘርተዋል፡፡
ሊድስ ከስድስት የመጨረሻ የሊግ ጨዋታ አንድም አልተሸነፈም፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ ከሊቨርፑል ጋር አቻ መለያየቱ የበለጠ በራስ መተማመኑን ከፍ ያደረገለት ቡድኑ ለዛሬው ፍልሚያ ዝግጁ ይመስላል፡፡
ዩናይትድ በአንፃሩ ከፍ እና ዝቅታውን ቀጥሎበታል፡፡ በ19ኛ ሳምንት ኦልድትራፎርድ ላይ ከዎልቭስ ጋር አቻ መለያየቱ ደጋፊዎችን አላስደሰተም፡፡
በዛሬው ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ አለማግኘት ሩበን አሞሪም ላይ ከምንጊዜውም በላይ ጫና ማሳደሩ አይቀርም፡፡ የኢንዞ ማሬስካን ስንብት የተመለከቱ የእንግሊዝ ብዙሃን መገናኝ አሞሪምስ? የሚል ጥያቄ እያነሱ ይገኛል፡፡
ሁለቱ ክለቦች ፕሪምየር ሊጉ እንደ አዲስ ከተዋቀረበት 1992 ጀምሮ 30 ጊዜ ተጫውተዋል፡፡ 17ቱ በማንችስተር ዩናይትድ አሸናፊነት ፣ 4ቱ ደግሞ በሊድስ ድል አድራጊነት ሲጠናቀቅ ዘጠኙ ነጥብ በመጋራት ተቋጭቷል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ