የ334 ዋሻዎች አሳሽ:- ናስር አህመድ

You are currently viewing የ334 ዋሻዎች አሳሽ:- ናስር አህመድ

AMN- ታኅሣሥ 26 / 2018 ዓ.ም

“የሀገር ብልጽግናና ሀብት በዋሻዎች ውስጥ ነው” የሚለው ናስር አህመድ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የዋሻ ተመራማሪ ሲሆን፣ በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ በዘርፉ ሁለተኛው ሰው ነው። በቅርቡ አፍሪካን ወክሎ በጀርመን ሀገር ተሸላሚ ሆኗል።

ናስር  አህመድ ከAMN ዲጂታል ጋር ባደረገው ቆይታ፤ “ሀገሬ በዚህ ሙያ እኔን ብቻ ስላላት፣ እንደ እኔ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሙያዎችን ማፍራት አለብኝ ብዬ በማሰብ ከውጭ ሀገራት የቀረቡልኝን የሥራ ዕድሎች ውድቅ አድርጌያለሁ” ብሏል።

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ ተወልዶ ያደገው ናስር፣ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ በዋሻ ተመራማሪነት እየሰራ ይገኛል።

በዘርፉ በኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርት እድል ባለመኖሩ ትምህርቱን በፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ጀርመን ሀገራት ተከታትሏል።

ናስር ባከናወናቸው የምርምር ሥራዎችም፤ እስከ አሁን 334 ተፈጥሯዊ ዋሻዎች ላይ ጥናት አካሂዷል።

ከእነዚህ ውስጥ በ200ዎቹ ላይ መጽሐፍ የጻፈ ሲሆን፣ ከ3 ዓመት በፊት “Caves in Oromia” የተሰኘ መጽሐፉን አስመርቋል።

ከጥንታዊ የኦሮሞ ስልጣኔ ጋር የተያያዙ በዋሻዎች ላይ የተከተቡ 133 ጽሑፎችን ያጠና ሲሆን፣ የ62ቱን ካርታና ፕላን አጠናቆ መጽሐፉን ለማስመረቅ 90 በመቶ ዝግጅት ላይ ይገኛል። በአጠቃላይ በሙያው እስካሁን 549 ዋሻዎች ላይ ጥናት አድርጓል።

በሐረርጌ የሚገኘውና “ናሲኦል” የተሰኘው ዋሻ በእርሱ ስም እንደተሰየመ ናስር ይገልጻል። ናስር እንደሚለው፤ “የዋሻ ምርምር እጅግ አደገኛና ፈታኝ በመሆኑ፣ ብዙ ጊዜ አሳሾች በስማቸው እንዲሰየም ይደረጋል” ብሏል።

ናስር ተመራማሪ ብቻ ሳይሆን ደራሲም ነው። እስካሁን በእንግሊዝኛ ቋንቋ 5 መጽሐፍትን የጻፈ ሲሆን፣ በቅርቡ “Sof Omer Cave and Prehistoric Rock painting” የተሰኘውን 350 ገጽ ያለው መጽሐፉን ያስመርቃል።

የናስር ትልቁ ራዕይ የዋሻ ምርምር ተቋም በማቋቋም አዳዲስ ተተኪዎችን ማሰልጠን ነው። ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍና ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ አቅርቧል።

የዋሻ ምርምር ከፍተኛ ወኔና ጥንካሬ እንደሚጠይቅ ናስር ይገልጻል። በአንድ ወቅት ለ10 ሰዓታት በእግር ተጉዞ ምርምር ካደረገ በኋላ፣ የሚተኛበት ቦታና ቤት በማጣቱ በሜዳ ላይ አድሮ እንደሚያውቅ ይናገራል።

ናስር ከናሲኦል (Naasi’ol) ዋሻ 18.6 ኪሎ ግራም የሚመዝን ናሙና ወስዶ ወደ ታይዋን ብሔራዊ ጂኦ-ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ መሄዱ ታውቋል። ዋሻው ከብዙ ሚሊዮን ዓመታት በፊት እንደተፈጠረ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ቀሪውን ክፍል ለመመርመርም ስልጠና እንደተሰጠው ገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው ሳይንቲስቶች ዋሻው የአፍሪካንና የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ ሁኔታ፣ እንዲሁም ግብርናን ጭምር ለመደገፍ የሚያስችል መሆኑን እንደተገለጸ ጠቅሶ፣ የምርምሩ ውጤት ወደፊት ይፋ እንደሚሆን ተናግሯል።

የዘርፉን አደገኛነት ሲያስረዳም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዋሻ ተመራማሪዎች መካከል 25 በመቶው ለሞት ይጋለጣሉ።

በተለይም ወደ ውስጥ በሚገቡበት ወቅት በገመድ ታግዘው እንደሚገቡና ውስጡ ውሃ ያዘለ፣ መሬቱ የሚንሸራተት፣ እንዲሁም ከ60-100 ሜትር የሚደርሱ ጥልቅ ጉድጓዶችን ስለሚይዝ መውደቅ፣ የድንጋይ መናድ እና የኦክስጅን እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ገልጿል። ከፍተኛ ሙቀትና ቅዝቃዜም ያጋጥማል።

በዋሻ መግቢያዎች ላይ እንደ ዘንዶና እባብ ያሉ አደገኛ ፍጥረታት፣ በአካባቢው ደግሞ ነብርና አንበሳ በብዛት ይገኛሉ።

ይህንን ሥራ ለመሥራት ሳንባ ጤናማ መሆን ያለበት ሲሆን፣ ከማንኛውም ዓይነት ሱስ ነፃ መሆን ለሕይወት አስፈላጊ መሆናቸውን አንስተዋል።

“ሀገራት ሁሉ ዋሻ የላቸውም፤ በኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን ኦሮሚያ ብቻ ነው በዋሻ የበለጸገችው” በማለት፣ በትግራይ፣ በአማራ እና በደቡብ ክልሎች ሲያጠናቸው የቆያቸው ዋሻዎች ግን መስፈርቱን አያሟሉም ብሏል።

በዩኔስኮ (UNESCO) እስካሁን የተመዘገበ ዋሻ ባይኖርም ሶፍ ዑመርን ለማስመዝገብ በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጿል።

ብቻዬን ሆኜ 334 ዋሻዎች ላይ ጥናት ማድረጉን የሚገልጸው ናስር፤ ነገር ግን እንደ እኔ ያለ (ተመራማሪ) ቢኖር ኖሮ የሀገራችንን ዋሻዎች ለዓለም ማሳየት ይቻል ነበር፤ እስካሁን ያልተገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ዋሻዎች አሉ ብሏል።

ስራው በግለሰብ ጥረት ብቻ ከግብ አይደርስም፤የእውቀት ሽግግር እንዲኖርና መሰል ባለሙያዎች እንዲሰለጥኑ ያለውን ጽኑ ፍላጎት ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም፣ “የሀገር ብልጽግናና ታሪክ በእነዚህ ዋሻዎች ውስጥ ተቀብሮ ይገኛል፤ ስለዚህ ሁሉም ዜጋ ሊንከባከባቸው ይገባል” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

በደራርቱ ተሬሳ









0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review