እውነተኛ ምሁርነት በማኅበረሰባዊ፣ በፖለቲካዊና በሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ የተሰናሰለ ሐሳብ መስጠት መቻል ነው

You are currently viewing እውነተኛ ምሁርነት በማኅበረሰባዊ፣ በፖለቲካዊና በሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ የተሰናሰለ ሐሳብ መስጠት መቻል ነው

AMN -ታኅሣሥ 27/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአልማዝ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ስለ ምሁርነት፣ ልሂቃንነት እና ብልህነት ጥልቅና አዲስ ዕይታ ያለው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው “ምሁርነት” በዲግሪ ብዛት ወይም በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመቆየት ብቻ የሚለካ ሳይሆን፣ ውስብስብ ሐሳቦችን የመፈተሽና የመጠየቅ ብቃት መሆኑን አብራርተዋል።

ይሀንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምሳሌ ሲያስረዱ፣ “መልህቅ ዘላለሙን ባህር ውስጥ ቢኖርም መዋኘት አይችልም” በማለት፣ በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ መኖር ወይም በታወቁ ዓለም አቀፍ ተቋማት መማር ብቻውን ምሁር እንደማያሰኝ ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ እውነተኛ ምሁርነት የሚለካው “ለመጠየቅ ባለው ዝግጁነት” እና በውስብስብ ሐሳቦች ውስጥ አልፎ ማኅበረሰባዊ መፍትሄን የማመንጨት አቅም ሲኖር ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንድ ሰው በአንድ የትምህርት ዘርፍ የተካነ ከሆነ እንደ ምሁር እንደሚቆጠር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እውነተኛ ምሁርነት ግን ከራሱ የትምህርት ክፍል ወጥቶ በማኅበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊና ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ የተሰናሰለ ሐሳብ መስጠት መቻል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዓለም ላይ በአብዛኛው ታላላቅ ግኝቶች የተመዘገቡት በዕድሜ ባለጸጋ በሆኑ አንባቢያን ሳይሆን በተፈጥሮ ብሩህ አእምሮ ባላቸው ወጣት ተመራማሪዎች መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ካጠራቀመችው ወረቀትና ዲግሪ ባለፈ “ዘመን ቀያሪና ማርሽ ቀያሪ” ሐሳቦችን የሚፈጥር የምሁር ማኅበረሰብ እንደሚያስፈልጋት አብራርተዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review