የባህር በር ጥያቄያችን እየተሳካ ያለ የመላው ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ነው – ብልጽግና ፓርቲ

You are currently viewing የባህር በር ጥያቄያችን እየተሳካ ያለ የመላው ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ነው – ብልጽግና ፓርቲ

AMN ታህሳስ 27/2018 ዓ.ም

የባህር በር ጥያቄያችን እየተሳካ ያለ የመላው ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ነው ሲል ብልጽግና ፓርቲ በሳምንታዊ መልዕክቱ ገልጿል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ያወጣዉ ሳምንታዊ መልእክት እንደሚከተለዉ ቀርቧል፡፡

የባህር በር ጉዳይ የኢትዮጵያ ቁልፍ ብሔራዊ ጥቅም እና የዘመናት የትግል ምክንያት ሆኖ የቆየ አጀንዳ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአፈጣጠርዋ እና በረጅም ታሪኳ የባህር በር ባለቤት ሆና የኖረች ታላቅ ሀገር ነች፡፡ ሀገረ-መንግሥቷም በየግዜው እየሰፋ የመጣ የመሬት እና ተፈጥሯዊ የባህር ግዛትና ሀብት ባለቤት በመሆን ከተለያዩ ሥልጣኔዎችና መንግሥታት ጋር ዓለምአቀፍ ግንኙነት መመሥረት የቻለ ጠንካራ እና ገናና ሀገረ-መንግሥት ነው፡፡

ከዚህ የኢትዮጵያ ቁመና መስተካከል ያቃታቸው አያሌ ጠላቶች ግዛቷና ሀብቷ በማሳጣት ሊያደሀይዋትና እንዳሻቸው ሊፈነጩባት ሲቋምጡ ኖረዋል፡፡ በተለይ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ በተፈጠረው የቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ባህር በር ግዛትና ሀብት ለመንቀጥ ከፍተኛ ግፊቶች ሲደርጉ ተስተዉሏል፡፡ ለዚህ ምክንያቱም ባህር በር ያላት ኢትዮጵያ ከተፅእኖአችንና ቁጥጥራችን ውጭ የሆነች የማትበገር ሀገር ትሆናለች የሚል ነበር፡፡

እነዚህ የሩቅና የቅርብ ጠላቶች በመላ ኢትዮጵያውያን እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ግዛቷ መውረር፣ ህዝቦችዋን ማስገበር፣ ሀብቷ መመዝበር እና ነጻነቷን መንጠቅ ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ግን ቅጥረኞችና የውስጥ ባንዳዎችን በመጠቀም ከአንድ ምዕተ-ዓመት በላይ ባሴሩት ሴራ ምክንያት ለጊዜውም ቢሆን ባህር በር አልባ እንድትሆን ማድረግ ተሳክቶላቸው ቆይቷል፡፡ በዚህ ምክንያትም ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ እና የሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጥገኛ ሆና እንድትቆይ ተደርጋለች፡፡ ይህ ሁኔታ ለማስቀጠልም የኢትዮጵያ ተፈጥራዊና ታሪካዊ የባህር በር መብት ባልተለመደ መልኩ ለማናናስና ለመድፈቅ ሲሞከር ቆይቷል፡፡

በህዝብ ገፊነትና በአመራር ሳቢነት እውን የሆነው ሀገራዊ ለውጥ ካነገባቸው ፍትሀዊ አጀንዳዎች የባህር በር ጥያቄ አንዱና ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡ መላ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው ባህር በር አልባ የሆነችበትን ሴራ አንቀበልም በማለት አጀንዳውን በአደባባይ በማቀንቀን ሲታገሉ ቆይቷል፡፡ የሀገራዊ ለውጡ አመራርም ከጅምሩ በዲፕሎማሲና በሰጥቶ-መቀበል መርህ ጥያቄው ሰላማዊ ምላሽ እንዲያገኝ ሲጥር ቆይቷል፡፡ በተለይ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ግንባር ቀደምና ቆራጥ መሪነት ከኤርትራ ጋር የነበረውን የሰላም ችግር በመፍታት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ የባህር በር እንዲኖራት ለማስቻል ከፍተኛ ሥራ ሰርተዋል፡፡

ይሁንና ከመጀመሪያውም ኢትዮጵያ የመልክዐ-ምድር እስረኛ ማድረግ እንደ ዋና ግባቸውና ጥቅማቸው የሚገነዘቡ የራሳቸውና የጎረቤቶቻቸው ልማት የማይፈልጉ የዜሮ-ድምር ፖለቲከኞች ይህ እንዳይሆን አሻፈረኝ ሲሉ ተስተዉለዋል፡፡

እንዲህም ሆኖ የኢትዮጵያ የባህር በር የመላ ኢትዮጵያውያን ፍትሀዊ ጥያቄ በመሆኑ ሊገታ የሚችል አልሆነም፡፡ አያሌ ሀገራት ይህንን የኢትዮጵያ ፍትሀዊ ጥያቄ እየደገፉ እና የመንግሥቷና የዜጎችዋና የተናበበ ቁርጠኝነት እያደነቁ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን በባህር በር ምክንያት ያጣችው ብሔራዊ ጥቅም የትየሌለ ሆኖ በመቆየት የአንዳንድ ሀገራት አጠቃላይ ገቢ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ላልተፈለገ ወጪ ከመዳረግ አልፎ እንደማንኛውም ሀገር ማስከበር የሚገባትን የደህንነትና የህልውና ጉዳዮችና ፍትሀዊ ጥቅሞች ሲያሳጣት ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር በር ባለቤትነት ለራስዋ፣ ለጎረቤት ሀገራት፣ ለቀጣናውና ለዓለም ጠቃሚ ነው፡፡ አስተማማኝና ዘላቂ የባህር በር ያላት ኢትዮጵያ የተቀላጠፈ ንግድ፣ የሚደጋገፍ ኢኮኖሚ ሌሎች የጋራ ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማሳካት ያስችላል፡፡ ይህም ከድህነት የተላቀቀች፣ ሰላምና መረጋጋት ያላት ሀገር በመፍጠር ለቀጣናውና ለዓለም ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡ አሁን የደረስንበት የዓለም አሰራርና አስተሳሰብም ይህንኑ ራዕይ የሚደግፍ ነው፡፡

በሉላዊነት/ግሎባላይዜሽን መርህ መሠረት ዓለም አንድ መንደር እየሆነች በመምጣት እንደ አንድ የጋራ መኖሪያ፣ ሀብቷ ደግሞ የሰው ልጆች በጋራና በፍትሀዊነት የሚጠቀሙት እንዲሆን ያበረታታል፡፡ ኢትዮጵያም ይህንኑ ዓለም የሚደግፈውና የሚገብረው አሰራር በመተግበር የባህር በር ፍላጎትዋ በሚገባት ልክ በዓለም መድረክ አቅርባ እያሳካችው ትገኛለች፡፡ ሌሎች የባህር በር የሌላቸው ሀገራትም የኢትዮጵያ ፈለግ በመከተል አጀንዳው እያነሱትና ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም አጀንዳው ከግዜ ወደ ግዜ የተለመደ እየሆነና እውን የመሆን ዕድሉ እየሰፋ መጥቷል፡፡

ለዚህም ነው ጥያቄው በመላ ኢትዮጵያውያን የጋራ አጀንዳ ከመሆን አልፎ በዓለም የሚደገፍ ፍትሀዊ ጥያቄ ለመሆን የበቃው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በታሪክ በምትታወቅበት የጋራ ተጠቃሚነትና የፍትሀዊነት መርህ የራስዋ ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ብቻ ሳይሆን ዓለም ለሁሉም ፍትሀዊ እንድትሆን ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡

ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚህ የታሪክ እጥፋት ላይ አሻራውን በደማቅ ቀለም ለመጻፍ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ “ለትውልድ ምንዳ እንጂ ዕዳ አናወርስም” ባልነው መሠረት የትውልድ ኀላፊነታችን እስከ መጨረሻ ግቡ ለማድረስ እንትጋ፡፡ “ያ ለሀገሩ የባህር በር መልሶ ያስገኘ አርበኛ፤ የብሔራዊ ጥቅምና የዓለም ፍትሀዊነት ዘበኛ፣ ቆራጥ፣ ሀገር ወዳድና ሰብዓዊ ትውልድ” ተብለን ለመዘከር ከምንግዜውም በላይ አጀንዳችንን በባለቤትነት አጥብቀን

ይዘን በጋራና በምልዓት እናሳካው፡፡

ብልፅግና ፓርቲ

ታህሳስ 27፤ 2018 ዓ/ም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review