ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ፣ በከተማችን በሚገኙ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ለሚኖሩ ከ300 ሺህ በላይ ምንም የገቢ ምንጭ ለሌላቸው፣ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸውና አቅመ ደካማ ወገኖቻችን የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብር አካሂደናል ብለዋል፡፡
የገና በዓል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልና የፍቅር መገለጫ በመሆኑ፣ በማዕድ ማጋራት ለተቸገሩ ወገኖቻችን ያለንን ፍቅር በተግባር የምንገልጽበት ነው። ይህ የበጎነት ተግባር የከተማችንን ጥልቅ የመረዳዳትና የአብሮነት እሴት ይበልጥ የሚያጸና ሲሆን፤ ዛሬም ጊዜያዊ ችግርን ለማለፍ እጅ ለአጅ ተያይዘን የምንቆም እና ለዘላቂ ልማት የምንተጋ ታላቅ ሕዝቦች መሆናችንን በተግባር ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል፡፡

በሁሉም በዓላት ካላቸው ላይ ለወገኖቻቸው በማካፈል፣ ለዚህ በጎ ተግባር መሳካት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አብረውን ለቆሙ ልበ-ቀና ባለሀብቶች፣ በትጋት ላስተባበሩ ወጣቶችና አመራሮች በራሴ፣ በከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም በተጠቃሚ ወገኖቻችን ስም ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
በዓሉ የፍቅር፣ የሰላምና የደስታ እንዲሆንላችሁ ከወዲሁ ከልብ እመኛለሁ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡