ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምሁራን ያከማቹትን እውቀት ወደ ሚጨበጥ ተግባር በመቀየር እና ሀገር የሚገነባ ትውልድ በመቅረጽ ረገድ የላቀ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአልማዝ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ማጠቃላያ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ምሁርነት በመጽሐፍ ክምችት ወይም በንባብ ብዛት ብቻ የሚለካ ሳይሆን፣ ችግር ፈቺ እሳቤዎችን በማፍለቅና ማህበረሰቡን በማነጽ ሊገለጽ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሳይንቲስት ሜሪ ኩሪ በ30 ዓመቷ ዓለምን የለወጠ የራዲዮ አክቲቪቲ ትርጓሜን መስጠቷን በምሳሌነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በወጣትነት ዕድሜ ቴክኖሎጂን የሚረዳና የሚተገብር ትውልድ ካልተፈጠረ ዘመን ቀያሪ እሳቤዎችን ማፍለቅ እንደማይቻል አስረድተዋል።
የምሁርነት መገለጫው ሀሳብ አክባሪና ሀሳብ አፍቃሪ መሆን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምሁራን ጥልቅ አሰላሳይ፣ ጠያቂ፣ ተንታኝና እውቀትን ወደ ተግባር በመለወጥ የማህበረሰቡን ኑሮ የሚያቀሉ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ምሁራን ራሳቸውን ተጽዕኖ ፈጣሪ ለማድረግ ከመስራት ባለፈ፣ ሀገርን የሚረከብ ተጽዕኖ ፈጣሪ ትውልድ የመፍጠር ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በፈተና ውስጥ አልፎ ሀገር የሚሰራ፣ ሀገር ወዳድና ተጽዕኖ ፈጣሪ ትውልድን መቅረጽ የምሁራን ዋነኛ የቤት ሥራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውታል።
ለተለያዩ ዘርፎች የተለያዩ የአስተሳሰብ ዓይነቶች አስፈላጊ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትልቅ ምስልን ለማየትና ለመተንበይ፣ ሥርዓትን ለመዘርጋት እንዲሁም ለአዳዲስ ፈጠራዎችና ለወደፊት ዕይታዎች ጠቃሚ የሆኑ አስተሳሰቦችን ማስረጽ ከምሁራን እንደሚጠበቅ አብራርተዋል፡፡
ምሁራን ስትራቴጂካዊና ፈጣሪ አስተሳሰብን እንዲያጎለብቱ እንዲሁም የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ትውልድ እንዲያፈሩም አሳስበዋል።
ምሁራን ዓለም አቀፋዊ ልምዶችን እንደ ወረደ ከመውሰድ ይልቅ፣ ወደ ሀገርኛ አሠራር በመቀየርና የእውቀት ዘርን በመዝራት ረገድ ተግተው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በበረከት ጌታቸው