የኢትዮጵያ ምሁራን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማየት የጋራ ትርክትን በመፍጠር ምሁራዊ አመራር መሥጠት እንደሚገባቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልፀዋች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማስመልከት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ጽሁፍ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽሁፋቸው ምሁራን ከድህነት የተላቀቀችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማየት የጋራ ትርክትን በመፍጠር ምሁራዊ አመራር መሥጠት አለባቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከድህነት አዙሪት አውጥቶ ወደ ተሟላ ብልጽግና ለማሸጋገር ምሁራን ሚናቸው የጎላ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ውጤታማ አመራር ለመስጠት በቅድሚያ ራስን ማሸነፍ ይገባል ብለዋል፡፡
መሪነት የሚጀምረው ከራስ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ምሁራን በውስጣቸው ያለውን ድምጽ ለይተው ማድመጥና ድል መቀዳጀት አለባቸው ብለዋል፡፡
ምሁራን የተሰጣቸውን ኃላፊነት፣ ዕውቀትና ተጽዕኖ ተጠቅመው ውጤታማ አመራር ለመስጠት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም አንስተዋል፡፡
ሀሳብ እንቅስቃሴ ይፈጥራል፤ እንቅስቃሴ ስርዓት ይፈጥራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ የምሁራን ሀሳብ ተቋም መፍጠር አለበትም ነው ያሉት፡፡