ለገና በዓል በቂ የምርት አቅርቦት መኖሩን የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ

You are currently viewing ለገና በዓል በቂ የምርት አቅርቦት መኖሩን የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ

AMN ታኅሣሥ 27/2018

በመዲናዋ ለገና በዓል በቂ የምርት አቅርቦት ማዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሀብተየስ ዲሮ ገለጹ፡፡

‎በከተማ ደረጃ የተቋቋመው የገበያ ማረጋጋት ፣ ህግ ማስከበር እና ኢትዮጵያ-አዲስ አበባ ታምርት ግብረ ሀይል የተለያዩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች ለህዝቡ እንዲቀርብ ማድረጉን ምክትል ኮሚሽነሩ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ አብራርተዋል፡፡

ከክልል ዩኒየኖችና ከፋብሪካዎች ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረትም የተለያዩ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል፡፡

ከሰብል ምርቶች ጋር በተያያዘ ከ40 ሺህ እስከ 50 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ጤፍ ፣ የስንዴና የበቆሎ ዱቄት በ11 ዩኒየኖችና በ154 የሸማች ማህበራት በኩል መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

የእንቁላልና ሽንኩርት አቅርቦትም ከሸገር ሲቲ ፣ ከፊንጫ አና ከወንጂ ስኳር ፋብሪካዎች እንዲሁም ከኤልፎራ ጋር በመተባበር ተመቻችቷል፡፡

የሽንኩርት ዋጋም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ቅናሽ የታየበት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በኪሎ ከ20 እስከ 30 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

የፓልም እና የፈሳሽ ዘይት አቅርቦት ከንግድ ስራ ድርጅት ጋር በመተባበር መቅረቡን በርበሬና ቅቤም ከ750 ብር ጀምሮ በሁሉም መጋዘኖች እንዲሰራጩ መደረጉን ምክትል ኮሚሽነሩ ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል፡፡

ከስጋ አቅርቦት ጋር በተያያዘም በከተማዋ በሚገኙ 267 የሸማቾች ስጋ ቤቶች አማካኝነት ከ2ሺህ በላይ በሬዎች ለቅርጫና ለለኳንዳ እንዲቀርቡ ተደርጓል።

የምርት ስርጭቱን ፍትሃዊ ለማድረግና የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል ኮሚሽኑ በ2ሺህ የሸማች ሱቆች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ሀብተየስ ዲሮ ገልጸዋል።

በ11ዱም ክፍለ ከተሞች 139 በሚሆኑ የሸማች ማህበራት አማካኝነት ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች ተከፍተው ለህዝቡ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

የህብረት ስራ ኮሚሽኑ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅና ህብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በቀንና በሌሊት እየሰራ መሆኑንም አረጋግጧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review