የአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የከተማዋን ደረጃ በሚመጥን መልኩ የሕንጻ ደረጃና ዲዛይንን እንዲያስጠብቅ፣ የማስታወቂያ አጠቃቀምን እንዲያሻሽልና በአገልግሎት አሰጣጥ የጀመራቸውን መልካም ውጤቶች አጠናክሮ እንዲያስቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሬትና ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የባለሥልጣኑን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ለመገምገም የመስክ ምልከታ አካሂዷል።
ቋሚ ኮሚቴው ምልከታውን ለአብነት በየካ ክፍለ ከተማ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ያካሄደ ሲሆን፣ ከቢሮ አደረጃጀትና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጀምሮ፣ በከፍተኛ ሁኔታ ዕድገት እያሳየች ያለቸውን አዲስ አበባን የሚመጥን የሕንጻ ግንባታ ደረጃን በማሟላት ረገድ በርካታ ለውጦች የታዩበት መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር አቶሜ አበበ ተናግረዋል።
ከከተማዋ ፈጣን ዕድገት ጋር የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠትና የሕንጻ ግንባታ እንዲሁም የማስታወቂያ ደረጃ እንዲሻሻል በቀጣይ ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ያሏቸውን ነጥቦችም ሰብሳቢው አንስተዋል።
የመሬትና ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባደረገው የመስክ ምልከታ ለውጥ የተመዘገበባቸውና ሊጠናከሩ ይገባል የተባሉትን ነጥቦች አስመልክተው የአዲስ አበባ ከተማ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሕይወት ሳሙኤል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ቋሚ ኮሚቴው “ቢታዩ” ያላቸው ሐሳቦች ባለሥልጣኑን ከፍ የሚያደርጉና የከተማዋን ደረጃ የሚያሻሽሉ በመሆናቸው፣ የተነሱትን ሐሳቦች በመውሰድ በተግባር እንደሚተረጉሟቸው ኢንጂነር ሕይወት ገልጸዋል።
በአንዋር አሕመድ