የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት እንደሚያስመዘግብና እ.ኤ.አ በ2044 ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአሁኑ ትውልድና የፖለቲካ እሳቤ ሀገርን በመገንባት ረገድ ልክ በየዘመኑ እንደተነሱት መሪዎች ሁሉ የራሱ የሆነ ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዳሉት አንስተው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በማስመልከት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አቅርበው ከታዳሚዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያውያን ምሁራን የውጭ ሀገራትን የዕድገት ተሞክሮዎች በቀጥታ ከመመኘት ይልቅ፣ በተግባር ሊተረጎሙ የሚችሉ ሀገር በቀል ሀሳቦችን ማመንጨት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ሀገሪቱ በያዘችው የዕድገት ጎዳና ከቀጠለች ይህንን ግብ ማሳካት እንደምትችል፣ በአንጻሩ ግን ከተግባር የራቀ ምኞት ብቻ ከሆነ ለሀገር ዕድገት እንቅፋት እንደሆነ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።
እንደ ወዳጅነት ፓርክ፣ የአንድነት ፓርክ እና የሳይንስ ሙዚየምን የመሰሉ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች በዜጎች ዘንድ አዲስ አስተሳሰብን ከመፍጠርም ባሻገር፣ ልማቱ የሀገርን ገጽታ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በያዝነው ዓመትም የኢኮኖሚ ዕድገቱ ባለ ሁለት አሀዝ እንደሚሆንና ይህም ሀገሪቱ በትክክለኛ የዕድገት ጎዳና ላይ መሆኗን እንደሚያሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመድረኩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፈረንጆቹ 2040 በአፍሪካ ሁለተኛው ባለግዙፍ ኢኮኖሚ፣ በ2044 ደግሞ በአፍሪካ ቀዳሚው እንደሚሆን ያላቸውን ጽኑ እምነት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
በወርቅነህ አቢዮ