የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች

You are currently viewing የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች

AMN ታኅሣሥ 28 ቀን 2018 ዓ.ም

በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተከናወነ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ የሚገቡ ሁለት ቀሪ ሀገራትን ዛሬ ይለያል፡፡

ምሽት 1 ሰዓት አልጄሪያ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሞሌይ ሃሰን ስታዲየም ይጫወታሉ፡፡ ምድብ አምስት ላይ የነበረችው አልጄሪያ ሦስቱንም ጨዋታዎቿን አሸንፋ ነው ወደ ጥሎማለፍ የገባችው፡፡

አልጄሪያ ምንም እንኳን ምድቧን በበላይነት ብታጠናቅቅም ፈታኝ ተጋጣሚ ደርሷታል፡፡ ምድብ አራት ላይ በግብ ክፍያ ብቻ ተበልጣ ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊ ኮንጎ ጠንካራ ስብስብ አላት፡፡

ኮንጎ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ካሜሩን እና ናይጄሪያን አሸንፋ ለ’’ኢንተር ኮንቲኔንታል’’ ጥሎ ማለፍ መድረሷ ይታወሳል፡፡

አልጄሪያ እና ዲ.ሪ ኮንጎ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ሲገናኙ የዛሬ ምሽቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ጋና እና ናይጄሪያ በጋራ ባሰናዱት 2000 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በምድብ ተገናኝተው 0ለ0 መለያየታቸው ይታወሳል፡፡

ምሽት 4 ሰዓት ላይ ኮትዲቯር ከቡርኪናፋሶ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡ የ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ኮትዲቯር አሁንም ጠንካራ እንደሆነች በምድብ ጨዋታዎቿ አሳይታለች፡፡

ምድብ ስድስት ላይ የነበረችው ኮትዲቯር ከሦስት ጨዋታ ሁለቱን አሸንፋ አንዱን አቻ በመውጣት በሰባት ነጥብ ቀዳሚ ሆና ነው ለጥሎ ማለፍ የደረሰችው፡፡ ቡርኪናፋሶ በአንፃሩ ከምድብ አምስት ሁለተኛ ሆና ነው ያለፈችው፡፡

ሁለቱ ሀገራት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 20 ጊዜ እርስ በእርስ ተጫውተዋል፡፡ ኮትዲቯር ዘጠኙን በማሸነፍ የበላይነቱን ትወስዳለች፡፡ ቡርኪና ፋሶ ሦስት ጊዜ ድል ቀንቷታል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review