የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ ማሳለፍ ይገባል

You are currently viewing የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲከበር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ ማሳለፍ ይገባል

AMN ታህሳስ 28/2018

የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ሲከበር ከጸሎትና ምስጋና ባለፈ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመደገፍ ማሳለፍ እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አባቶች ነገ የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም፥ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር በምስጋና ብቻ ሳይሆን በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን በመርዳትና በመደጋገፍ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዚሁ ወቅት፤በዓሉ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር በተግባር የገለጸበት ነው ብለዋል።

የእምነቱ ተከታዮችም የልደት በዓልን ሲያከብሩ ለፈጣሪ ጸሎትና ምስጋና ከማቅረብ ባሻገር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመተሳሰብ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚህም በተለያየ ምክንያት የምግብ፣የልብስና መጠለያ እጥረት የገጠማቸውን ወገኖች በማገዝ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ መደገፍና ማገዝ እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ በበኩላቸው፤ የኢየሱሰ ክርስቶስ ልደት ሲከበር አቅመ ደካማና ረዳት የሌላቸውን ወገኖች በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይም በዓሉ ሲከበር ሕሙማንን በመጠየቅ፣አቅመ ደካማና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ወገኖች ካለን በማከፈልና የታረዙትን በማልበስ ማሳለፍ ይገባናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ፀሐፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያና በተለያዩ ሀገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የ2018 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል የደስታና የፍቅር እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ የእግዚአብሔርን ይቅር ባይነትና ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ፍቅር የሚያሳይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ልዩነቶችን በእርቅ በመፍታት ለዘላቂ ሰላም እንትጋ ያሉት ቄስ ጀምበሩ፥የወንጌል አማኞች ፍቅርንና ሰላምን ከማወጅ ውጭ ሌላ መለኮታዊ ተልዕኮ የለንም ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review