ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ጋር በመሆን፣ የክረምት በጎ አድራጎት መርሃ ግብርን ወደ ላቀ ከፍታ ያሸጋገረውን የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደርን በይፋ መርቀናል ሲሉ ገለጸዋል፡፡
ይህ ሞዴል መንደር በ7 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ቤት ሁለት መኝታ ክፍሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ አምስት ክፍሎች እንዲኖሩት ተደርጎ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ ነው።

መንደሩ በቤተሰብ ደረጃ ለ150 ዜጎች ምቹና ጽዱ መኖሪያ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦቱም የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የኤሌክትሪክና የሶላር ኃይል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስፍራ እና የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡
የነዋሪዎቹን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት ለማሻሻል መንደሩ የምርትና የገበያ ሰንሰለትን ያካተተ የተቀናጀ አሰራርን ዘርግቷል። ይህ የልማት ስራ የወተት ላሞች እና የዶሮ እርባታን እንዲሁም የጓሮ አትክልት ልማትን አጣምሮ የያዘ ሲሆን፣ እስከ መገበያያ ስፍራ የሚደርስ የተቀናጀ የንግድ ሰንሰለት ተፈጥሮለታል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡