በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ታኅሣሥ 25ን የልደት በዓል አድርገው በታላቅ ድምቀት ቢያከብሩም፣ ለሌሎች በርካታ ሀገራት ግን “ገና” ገና ነው።
እነዚህ ሀገራት የጎርጎርዮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር ወደ ጎን በመተው፣ ጥንታዊውን የጁሊያን ቀመር በመከተል በዓሉን በፈረንጆቹ ጥር ወር (በኢትዮጵያ ታኅሣሥ 29) ያከብሩታል።
ከበረዷማዋ ሩሲያ እስከ ወበቃማዋ ግብፅ፣ ከጆርጂያ ተራራማ መንደሮች እስከ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ድረስ የልደት በዓል በልዩ ልዩ ባሕላዊ ቀለማት ደምቆ ይከበራል።

የሰላቪክ ሀገራት መንፈሳዊ ድባብ
በሩሲያ፣ ቤላሩስ እና ሰርቢያ የገና በዓል ከሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት ባለፈ ጥልቅ ብሔራዊ ትርጉም አለው።
በሩሲያ እና ቤላሩስ ከጥር 1 ጀምሮ የሚዘልቀው የሳምንት ዕረፍት ማሳረጊያው የገና በዓል ነው።
በእኩለ ሌሊት በታላላቅ ካቴድራሎች የሚካሄደው የቅዳሴ ጸሎት ምዕመናንን በአንድነት ያቆማል።
በሰርቢያ እና ሞንቴኔግሮ ግን ነገሩ ለየት ይላል
በዓሉ “ቦዢች” ይባላል፤ እዚህ ጋር “ባድንያክ” የተሰኘ ድንቅ ወግ አለ፤ ቤተሰቦች የኦክ ዛፍ ቅርንጫፍን ወደ ቤታቸው በማስገባት እሳት ያነድዳሉ።
ይህ እሳት በቤተልሔም በረት ውስጥ እረኞች ሕፃኑን ኢየሱስን ለማሞቅ ያነደዱት እሳት ምሳሌ ተደርጎ ይወሰዳል።

የጥንታውያኑ ኮፕቶች ገና በግብጽ
በግብጽ የሚገኙ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች (ኮፕቶች) በዓሉን የሚያከብሩት ከ43 ቀናት ጥብቅ ጾም በኋላ ነው። በዓሉ በሀገሪቱ በሕግ የታወቀ ብሔራዊ በዓል ሲሆን፣ ከጸሎት በኋላ የሚቀርበው ማዕድ ልዩ ነው።
“ፋታ” የተሰኘው ከዳቦ፣ ከሩዝ እና ከሥጋ የሚዘጋጀው ባህላዊ ምግብ የበዓሉ ዋነኛ ድምቀት ነው፤ ይህ ምግብ ለግብጻውያን የጾም መፍቻ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ አንድነት ምልክትም ነው።
“አሊሎ” – የጆርጂያ የጎዳና ላይ መዝሙር

ጆርጂያ ገናን የምታከብረው በታላቅ የጎዳና ላይ ሰልፍ ነው።
“አሊሎ” በሚባለው በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ ሰዎች ባህላዊ አልባሳቶቻቸውን ለብሰው፣ ሃይማኖታዊ መዝሙራትን እየዘመሩ በከተማው ይዞራሉ።
ይህ ጉዞ ደስታን ለመግለጽ ብቻ ሳይሆን ለችግረኞች እና ለሕፃናት የሚሆን ምግብና ገንዘብ የሚሰበሰብበት የበጎ አድራጎት መድረክም ነው።
የብዝሃነት ተምሳሌቶቹ ካዛኪስታን እና ሞልዶቫ
በመካከለኛው እስያ የምትገኘው ካዛኪስታን ምንም እንኳን የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚበዙባት ሀገር ብትሆንም፣ ለሃይማኖቶች እኩልነት እና ለብዝሃነት ክብር ሲባል ጥር 7ን ብሔራዊ የበዓል ቀን አድርጋ ታከብራለች።
ሞልዶቫ ደግሞ በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት ለየት ባለ መልኩ ታኅሣሥ 25ን እና ጥር 7ን – ሁለቱንም የገና ቀናት በይፋ የምታከብር ልዩ ሀገር ናት።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ፡ የጥንታዊነት ማህተሞች
ወደ አፍሪካ ቀንድ ስንመጣ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ጎረቤታችን ኤርትራ የራሳቸውን የቀን አቆጣጠር ጠብቀው በዓሉን በታላቅ መንፈሳዊነት ያከብራሉ።
በኢትዮጵያ “ገና” ሃይማኖታዊ በዓል ብቻ ሳይሆን የሀገራችንም ባህል ጭምር ነው። ነጭ የሀገር ባሕል ልብስ እና ነጠላ የለበሱ ምዕመናን በቤተክርስቲያን የሚያድሩበት፣ ካሕናት በያሬዳዊ ወረብ የሚያሸበሽቡበት ድባብ ለየት ያለ ነው።
በተለይ በታሪካዊቷ ላሊበላ የሚከበረው “ቤዛ ኩሉ ዓለም” የልደት በዓል በሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን የሚስብ ድንቅ ክስተት ነው።
በእረኞች ትውፊት ላይ የተመሰረተው “የገና ጨዋታ” ደግሞ ለበዓሉ ተጨማሪ ስፖርታዊ እና ባህላዊ ለውጥ ይሰጠዋል።
በኤርትራም በተመሳሳይ መልኩ ቤተሰብ በማዕድ ተሰብስቦ፣ እንደ ዶሮ ወጥ ያሉ ባሕላዊ ምግቦችን በመመገብ በዓሉን በፍቅር ያሳልፋሉ።
የገና በዓል የሚከበርበት ቀናቱ፣ ባሕላቱም፣ የአከባበር ሥነ ስርዓቱም ቢለያዩም፣ በኢትዮጵያዊያን ታኅሣሥ 29 በሌሎቹ ሀገራት ደግሞ በጥር ወር የሚከበረው በዓሉ የጋራ ትርጉም ነው ያለው፡- እሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ መወለድ ነው።
በታምራት ቢሻው