ከካፌ ዕቃ አጣቢነት እስከ ዓለም የከፍታ ዝላይ ክንድ፦ የኒኮላ ኦሊስላገርስ የጽናት ጉዞ

You are currently viewing ከካፌ ዕቃ አጣቢነት እስከ ዓለም የከፍታ ዝላይ ክንድ፦ የኒኮላ ኦሊስላገርስ የጽናት ጉዞ

AMN – ታኅሣሥ 30/2018 ዓ.ም

በተፈጥሮ የተሰጠን ነገር ብቻው ለስኬት አያበቃም፤ ስኬት የሚመጣው ካልተገደበ ሕልም እና እንደብረት ከጠነከረ ጽናት ነው። ይህንን እውነት በተግባር ያስመሰከረችው አውስትራሊያዊቷ የከፍታ ዝላይ ንግስት ኒኮላ ኦሊስላገርስ (ቀድሞ ኒኮላ ማክደርሞት) ናት። ዛሬ ዓለም በክብር የሚያያት ይህቺ እንስት፣ የስኬት ማማ ላይ ከመውጣቷ በፊት ግን የፈተናን እሳት አልፋለች።
ከመጨረሻነት ወደ ቀዳሚነት
ታኅሣሥ 28 ቀን 1996 በአውስትራሊያ ምድር የተወለደችው ኒኮላ፣ በልጅነቷ ረጅም ቁመት ቢኖራትም በስፖርቱ ረገድ ግን “ጎበዝ” የምትባል አልነበረችም። ይልቁኑ የሰውነት እንቅስቃሴን ለማከናወን የምትቸገርና ተስፋ የማይጣልባት ነበረች። ነገር ግን በ7 ዓመቷ በትምህርት ቤት አትሌቲክስ ስትጀምር ውስጥዋ የነበረው ድንቅ ብቃት እንደ እሳተ ጎመራ መፈንዳት ጀመረ። የብረት ኳስ ውርወራን ጨምሮ እስከ 200 ሜትር ሩጫ ድረስ ውድድሮችን በአሸናፊነት በመጨረስ የወደፊት ማንነቷን ማሳዬት ጀመረች።


የማስታወሻ ደብተሯ ምስጢር
ኒኮላን ከሌሎች አትሌቶች ለየት የሚያደርጓት ሁለት ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው ዝላይዋን በጨረሰች ቁጥር የምትይዘው “የስኬት ማስታወሻ ደብተር” ነው። በእያንዳንዱ ዝላይ ራሷን ከ10 ነጥብ እየመዘነች ስህተቷን የምታርምበትና ስሜቷን የምታሰፍርበት ይህ ደብተር፣ ለስኬቷ እንደ ኮምፓስ ሆኖ አገልግሏታል። ሁለተኛውና ዋናው ደግሞ ጠንካራ እምነቷ ነው። በውድድር ሜዳ ላይ የምታሳየው ሰላምና መረጋጋት ምንጩ እምነቷ እንደሆነ ሳትሸሽግ ትናገራለች።
ካፌ ውስጥ የታጠበው ሕልም
የኒኮላ ታሪክ እጅግ ልብ የሚነካ የሚሆነው የትናንት ማንነቷን ስታስታውስ ነው። ዛሬ በሚሊዮኖች ፊት በኩራት የምትቆመው እንስት፣ በአንድ ወቅት በአንድ ካፌ ውስጥ ዕቃ በማጠብ ትተዳደር ነበር። እጆቿ ሳሙናና ውሃ ውስጥ ሆነውም ልቧ ግን ስለከፍታ ዝላይ ማማ ያልም ነበር። “ያ የካፌ ዕቃ አጣቢነት ጉዞ ነው ለዛሬው ዓለም አቀፍ ዝና ያበቃኝ” ስትል ጽናቷን ምስጢር ትናገራለች።
የስኬት ማማ ላይ መድረስ
የኒኮላ የድል ጉዞዎች ታሪክን የሚቀይሩ ነበሩ፦

በቶኪዮ 2020 እና በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆነች። በ2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የከፍታ ዝላይ የወርቅ ሜዳሊያ አሸነፈች። በተጨማሪም የኦሽኒያ የከፍታ ዝላይ ክብረ ወሰን ባለቤት እና የ2024 የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮን።

በቅርቡ ደግሞ የ2025 የዓመቱ ምርጥ አትሌት (Field Athlete of the Year) ተብላ በመመረጥ ስሟን በወርቅ ቀለም በታሪክ መዝገብ ላይ ማስፈር ችላለች።
ከካፌ ዕቃ አጣቢነት ተነስታ ዓለምን እስካስደነቀው የከፍታ ዝላይ ድረስ የተጓዘችው የኒኮላ ኦሊስላገርስ ታሪክ፤ ጽናት ካለ የማይደረስበት የከፍታ ማማ እንደሌለ ትልቅ ማሳያ ነው።
ምንጭ፦ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ
በቶለሳ መብራቴ ተዘጋጀ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review