ኔስትሌ (Nestle) የተባለ ድርጅት ከሚያመርታቸዉ የጨቅላ ህጻናትና የታዳጊ ህጻናት ምግብ ምርቶች ዉስጥ አንዱ ምርቱ ላይ ባጋጠመ ብክለት ከተሰራጨባቸዉ ሀገራት ጥቅም ላይ እንዳይዉሉ እና ከገበያ እንዲሰበሰቡ የጥንቃቄ መልክት ማስተላለፉን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ባለስልጣኑ እንዳስታወቀው፣ ኔስትሌ (Nestle) የተባለ ድርጅት ከሚያመርታቸዉ የጨቅላ ህጻናትና የታዳጊ ህጻናት ምግብ ምርቶች ዉስጥ የምርት መለያ(Brand)፦ NAN Special Pro HA 0-12 ፣ የባች ቁጥሩ 51660742F3 ፣ በፈረንጆቹ ጁን 15 ቀን 2025 የተመረተ እና በዲሴምበር15 ቀን 2026 አገለግሎቱ የሚያበቃ ክብደቱ ባለ 800 ግራም የሆነ ምርቱ ላይ ባጋጠመ ብክለት ከተሰራጨባቸዉ ሀገራት ጥቅም ላይ እንዳይዉሉ እና ከገበያ እንዲሰበሰቡ የጥንቃቄ መልክት በታኅሣሥ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ልኳል፡፡
በመሆኑም ምንም እንኳን ምርቱ በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ተመዝግቦ የገበያ ፈቃድ የተሰጠዉ እና ጥቅም ላይ እንዲዉል የተፈቀደለት ባይሆንም፣ በተለያየ መልኩ ገበያ ላይ የሚኖርበት ሁኔታ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰባችን ከላይ የተጠቀሰዉን ምርት እንዳይገዛና ጥቅም ላይ እንዳያዉል ሲል ባለስልጣኑ አሳስቧል፡፡
ምርቱን በማንኛዉም መንገድ ለህብረተሰቡ ማቅረብ የተከለከለ መሆኑንም የገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም ምርቱን የያዘ ወይንም ያገኘ ማንኛዉም አካል ለይቶ በማስቀመጥ ለባለስልጣኑ እንዲያሳውቅ አሳስቧል፡፡
እንደ ድርጅቱ መግለጫ በምርቶቹ ላይ ያጋጠመው ችግር ባሲለስ ሴረስ በተባለ የባክቴሪያ ዝርያ የሚከሰት Cereulide የተባለ መመረዝ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በዚህ ዙሪያ በሌሎች የድርጅቱ ምርቶች ላይ የማጣራት ስራ እየተሰራ ስለሆነ ተጨማሪ መረጃ እንደደረሰን የምናቀርብ ይሆናል ሲል የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡