የትውልድ ድምፅ የሆነው ኤ ኤም ኤን ሲያካሂደው የቆየውና ለአንድ ዓመት የዘለቀው አዲስ ታለንት ሾው፣ በአድዋ ድል መታሰቢያ በተካሄደው ደማቅ የፍጻሜ ሥነ-ሥርዓት መቋጫውን አግኝቷል።
በሰባት ምዕራፎች ተከፍሎ ሲካሄድ የቆየው ይህ ውድድር፣ በልዩ ይዘቱና በአቀራረቡ አዳዲስ ጥበበኞችን ለሀገር አስተዋውቋል።
በማጠቃለያ መድረኩ ላይ የተገኙ ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ለውድድሩና ለተወዳዳሪዎቹ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
የሙዚቃ መምህር እና ባለሙያ ሰርፀ ፍሬስብሀት በሰጡት አስተያየት፣ እንዲህ ያሉ የተሰጥኦ ውድድሮች እያደጉና እየበለጸጉ መምጣታቸውን ገልጸው፣ ኤ ኤም ኤን ለዚህ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“ዛሬ ያየናቸው የጥበብ ሥራዎች በየራሳቸው ሚዲየም የቀረቡበት መንገድ በጣም የሚያስደስት ነው” ብለዋል።
ውድድሩ አንዱን ጥበብ (አርት) ከሌላው ለማበላለጥ ሳይሆን፣ “ማን ስራውን ስሜት በሚነካ መንገድ የበለጠ ተግብሮታል?” በሚል መለኪያ መመዘኑን የዳኝነቱን ሚዛናዊነት ገልጸዋል።
ተወዳዳሪዎቹ በዳኞች አስተያየት እየታረሙና እየታነጹ መምጣታቸው፣ እንዲሁም ያቀረቧቸው የራሳቸው የፈጠራ ሥራዎች አስደናቂ እንደነበሩ መስክረዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ኤፍሬም ለማ በበኩላቸው፣ አብዛኞቹ ተወዳዳሪዎች ሕፃናትና ታዳጊዎች መሆናቸው ለከተማዋ የጥበብ ተስፋ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።
አያይዘውም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ለወጣቶች ተሰጥኦ ልዩ ትኩረት መስጠቱ ለጥበብ እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ለጥበብ ባለሙያዎች ምቹ የሆኑ በርካታ ስፍራዎችን ያዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፣ ኤ ኤም ኤን ደግሞ እነዚህን ውጤታማ ታዳጊዎች በማዘጋጀት ረገድ እያከናወነ ያለውን ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲስ ታለንት ሾው ከውድድርና ከሽልማት ባለፈ፣ ለሀገሪቱ የጥበብ ዘርፍ አዲስ ተተኪዎችን ያፈራ መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።
ይህ ታላቅ ዝግጅት በከተማዋ ለጥበብ የተሰጠውን ትኩረትና ቀጣይ ብሩህ ተስፋ አመላካች ሆኖ አልፏል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ