የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጋር በመቀናጀት የተጀመረው ይህ ከተማ አቀፍ ንቅናቄ ጥር ወርን በሙሉ የሚከናወን መሆኑ ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ታረቀኝ፣ ንቅናቄው በከተማዋ የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስችል ግንዛቤ የመፍጠር እና ጠንካራ የቁጥጥር ተግባራት የሚከናወኑበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ንቅናቄው ከጥር 1 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ መሆኑን ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በጥር ወር ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የሚከሰትበት እንዲሁም የተለያዩ የአደባባይ በዓላት የሚካሄዱበት እና በርካታ ማህበራዊ ኩነቶች የሚፈፀሙበት በመሆኑ ወሩ መመረጡን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ተወካይ ኮማንደር ኩራ ሙሉጌታ፣ በንቅናቄው የአሽከርካሪዎችንና እግረኞችን የመንገድ አጠቃቀም ግንዛቤ የሚያሻሽል ተግባራት በመገናኛ ብዙሃን፣ በትምህርት ቤቶች እና በሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም በአውራ ጎዳናዎች ላይ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
ጠጥቶ ማሽከርከርም ሆነ ከተፈቀደ ፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከርን ጨምሮ የወጡ የመንገድ ደህንነት ህጎችን ለማስከበር የሚያስችል ጠንካራ የቁጥጥር ስራ እንደሚከናወንም ኮማንደር ኩራ ሙሉጌታ ተናግረዋል።
በንቅናቄው ከግንዛቤ ፈጠራ ጎን ለጎን ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ አደጋ የሚከሰትባቸው ስፍራዎችን በመለየት አስፈላጊ የሆኑ የምሕንድስና ስራዎች የሚከናወኑበት መሆኑ በንቅናቄ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
በታምሩ ደምሴ