ርቀት ያልገደበው ታማኝነት፦ 300 ሺህ ብር በስሕተት የደረሳት ወጣት ያሳየችው አስደናቂ ተግባር

You are currently viewing ርቀት ያልገደበው ታማኝነት፦ 300 ሺህ ብር በስሕተት የደረሳት ወጣት ያሳየችው አስደናቂ ተግባር

AMN  ጥር 01 ቀን 2018 ዓ.ም

“አማን አውለኝ” ብለው ለዕለት ስራዎ ወደ ስራ ቦታዎ ባቀኑ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ፣ የስልክዎ መልዕክት ሳጥን ባልተጠበቀ ዜና ቢሞላ ምን ይሰማዎታል? ያውም ከበዓል ማግስት በመሆኑ የዘገየ የእንኳን አደረሰዎ መልዕክት መስሎዎት የከፈቱት ጽሑፍ “300,000 (ሶስት መቶ ሺህ) ብር ወደ ሒሳብዎ ገብቷል” የሚል ቢሆንስ?

ዛሬ በአዲስ አበባ አያት አካባቢ ነዋሪ የሆነችው ወጣት እመቤት መኮንን (በቅርቦቿ እሙ እየተባለች የምትጠራው)፣ የብዙዎችን ቀልብ የሳበና “ደግ ደጎችን ያብዛልን” የሚያስብል ድንቅ የታማኝነት ተግባር ፈጽማለች።

“የሰው ሀቅ ለኔ አይገባም”

ወጣት እመቤት ስለሁኔታው ለኤ ኤም ኤን (AMN) ዲጂታል ስታስረዳ፥ “ዛሬ ማለዳ ወደ ሥራ ስገባ ወደ ስልኬ የገባው መልዕክት ከወትሮው የተለየ ነበር። ወደ ባንክ አካውንቴ ሶስት መቶ ሺህ ብር መግባቱን የሚገልጽ መልዕክት አየሁ። ከማን እንደገባ ሳረጋግጥ የማላውቀው ሰው መሆኑን አወቅኩ፤ ወዲያውኑም ‘ይህ የሰው ሀቅ ነው፣ የኔ አይደለም’ በማለት ለራሴ ነገርኩት” ስትል በሳቅ ታጅባ በታማኝነት ተናግራለች።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ገንዘቡን በስሕህተት የላከው ግለሰብ ደውሎ ሲያነጋግራት፣ ወጣት እመቤት ለአፍታም ሳታመነታ ገንዘቡን ለመመለስ ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻለታለች።

የኅሊና ዕረፍትና የማኅበረሰብ እሴት

“እኔም በላቤ የምኖር ሰው ነኝ። ሰው በላቡ ለፍቶ ያገኘውን ገንዘብ በስሕተት ወደ ሌላ ሰው መላክ ሊያጋጥም ይችላል፤ የራስ ያልሆነን ነገር መመለስ ግን ለኅሊና ዕረፍት ነው” የምትለው ወጣት እመቤት፣ ድርጊቷ ያደገችበት ማኅበረሰብና የቤተሰቧ ዕሴት ውጤት መሆኑን ተናግራለች።

ከአላማጣ እስከ አዲስ አበባ

የገንዘቡ ባለቤት ወጣት መሐመድ መኪ በአላማጣ ከተማ በሕንጻ መሳሪያ መደብር ውስጥ እየሠራ የሚተዳደር ወጣት ነው። ዛሬ ማለዳ ለወንድሙ እንዲላክለት የሰጠው 300 ሺህ ብር፣ በስሕተት መዳረሻው ወደማያውቀው የሒሳብ ቁጥር መግባቱን ሲረዳ ወዲያውኑ ወደ ንግድ ባንክ በመሄድ ጉዳዩን አስመዝግቧል።

መሐመድ ስለ ሁኔታው ሲገልጽ፤ “ገንዘቡ አዲስ አበባ ወደምትገኝ አንዲት ግለሰብ መግባቱ ተነገረኝ። ከባንክ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ስልክ ስንደውልላት፣ ወጣቷ ለአፍታም ሳታመነታ ገንዘቡን መለሰችልኝ። ከሁሉም በላይ ለመመለስ ያሳየችው ፍጥነትና ትብብር ለሌሎች ትልቅ አርዓያ የሚሆን ነው” ብሏል።

“አላህ ሀቋን ይክፈላት”

ወጣት መሐመድ “ደውለን ስናናግራት የሰጠችን ምላሽ እምነቷንና ታማኝነቷን እንድገነዘብ አድርጎኛል። ‘እኔም በላቤ የማድር ሰው ነኝ፣ የሰው ሀቅ ለማንም አይጠቅምም’ ማለቷ በእጅጉ አስከብሯታል። አላህ ሀቋን ይክፈላት” በማለት ምስጋናውን አቅርቧል።

ውድ የኤ ኤም ኤን ቤተሰቦች፥ እናንተስ ወጣት እመቤት (እሙ) ካደረገችው ተግባር ምን ተረዳችሁ? የታማኝነት ዋጋውስ ስንት ነው ትላላችሁ?

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review