“ኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በሁኔታዎች ወደማይለዋወጥ የስትራቴጂክ ትብብር አድጓል”
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት በታሪክ ማህደር ውስጥ ሲፈተሽ፣ በጋራ ተጠቃሚነትና በመከባበር ላይ የጸና የሁለት ታላላቅ ስልጣኔዎች ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነት ስለመሆኑ እንረዳለን። ይህ ለዘመናት የዘለቀ ጥብቅ ትስስር፣ በጊዜ ሂደት እየጎለበተ መጥቶ ዛሬ ላይ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፎች የማይበጠስ ጠንካራ ሰንሰለት ፈጥሯል። ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬው ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ድረስ ያለው ጉዞ፣ በሀገራት መካከል ለሚኖር ወዳጅነት እንደ ተምሳሌት የሚጠቀስ ህያው ምስክር ተደርጎም ሊወሰድ የሚችል ነው።
በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ዘመናዊውና ይፋዊው የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1970 ይሁን እንጂ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያመለክቱት፣ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ ግንኙነት ወደ ኋላ ወደአክሱም ዘመን ድረስ እንደሚሄድ ነው፡፡ ዘመናዊው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በዘመናት መካከል እያደገ መጥቶ ትብብሩ ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ደርሷል፡፡ አሁን ደግሞ ግንኙነቱ ከኢኮኖሚ ባለፈ ወደ “ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት” አድጓል።
የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ሰሞነኛው የኢትዮጵያ ጉብኝት የዚሁ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ዋንግ ዪ፣ የፈረንጆቹን የ2026 አዲሱን ዓመት የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን በአፍሪካ ለመጀመር ታህሳስ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ነበር አዲስ አበባ የገቡት፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ እና ቻይና ለአስርት ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸውና ይኽ ግንኙነትም በቅርቡ በሁኔታዎች ወደማይለዋወጥ የስትራቴጂክ ትብብር አድጓል ብለዋል።
ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር በጽናት በሚጓዘው የኢትዮጵያ እና ቻይና የመንግሥት እና ሕዝብ ግንኙነት ላይ ተነጋግረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ “የተለያዩ የልማት ትብብር ርዕሰ ጉዳዮች ለማከናወን ያለንን ጽኑ አቋም በማስቀጠል ላይ ውይይት አድርገናል።” ሲሉም አክለዋል። አያይዘውም በኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ መሠረተ ልማት፣ የኃይል አቅርቦት እና ትራንስፖርት ብሎም አዲስ በመፈጠር ላይ ባሉ እንደኢ-ኮሜርስ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የአረንጓዴ ኃይል ልማት ላይ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ለማጠናከር ውይይት ስለመደረጉም አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫም በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር ቀጣይነት ባለው መልኩ እያደገ በመምጣቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡ በዚህም የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ ከ13 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የበለጠ ሲሆን፣ ይህም ቻይና ኢትዮጵያን ዋነኛ የንግድ አጋር በማድረግ ግንኙነቷን እያጠናከረች መሆኑን ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያም ከቻይና የምታስገባው ምርት በተጠናቀቀው ዓመት መጀመሪያ ላይ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ በመጋቢት ወር ብቻ 1 ነጥብ 57 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 22 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እንደሚለው የውጭ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰትም ጠንካራ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፣ ቻይና በማኑፋክቸሪንግ፣ በመንገድና ሕንጻ ፕሮጀክት ግንባታዎች ላይ በመሰማራት ግንባር ቀደም ሆና እየሰራች ነው፡፡ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞን የሚያፋጥኑ የመሠረተ ልማትና የፋይናንስ ተደራሽነት ማስፋፋት በተለይ ከባቡር ሐዲድ ዝርጋታ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች እስከ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ድረስ የተገኙ ስኬቶች የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ አጋርነት አጠናክሯል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የሁለትዮሽ ኢኮኖሚ አጋርነት ለሁለቱም ሀገራት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡ የኢትዮጵያን የዲጂታል ራዕይ ወሳኝ የሆኑ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ እና የገበያዎች መዳረሻ እንድትሆን እድል የሚያሰፋ ሲሆን፣ ለቻይና ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ እንደ መግቢያ በር ሆና ታገለግላለች፡፡ በተለይ ከቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ጋር በማጣጣም የቻይና የረጅም ጊዜ የጋራ ልማት ራዕይን እውን ያደርጋል፡፡
በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ይፋ የተደረገው ኢትዮጵያ እና ቻይና የኢትዮ ጅቡቲን እና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መስመርን ማዘመን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ተስማሙ የሚለው ዜናም የዚሁ የሁለቱ ሀገራት ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነት ውጤት ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ካደረጉት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር ተወያይተው የኢትዮ- ጅቡቲንም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡርን ማዘመን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መስማማታቸውን የመካከለኛው ምሥራቅ፣ የእስያ እና ፓስፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዳዋኖ ከድር ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንጆቹ 2023 ቤጂንግን ሲጎበኙ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የማይናወጥ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ሆነው በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውንም አምባሳደር ዳዋኖ አስታውሰዋል። ሁለቱ ሚኒስትሮች ባደረጉት ውይይት ፓለቲካ እና ልማትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጄኔራል አምባሳደር ዳዋኖ ከድር ገልጸዋል።
ውይይቶቹን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባወጡት የጋራ መግለጫ በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ላይ የተላለፉ ውሳኔዎችን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ እና ቻይና ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን እንደ ተሞክሮ በመውሰድ የቻይና-አፍሪካ የጋራ ማሕበረሰብን ለመገንባትና ሁሉን አቀፍ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማምተናልም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአንድ ቻይና መርህን እና የቻይናን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት እንደምታከብር በመግለጽ የቻይና መንግሥት ሀገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ አረጋግጣለች፡፡
ቻይና በበኩሏ የአፍሪካ ሀገራት ቀጣናዊ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርባለች፡፡ በተለይም የባሕር በር ተደራሽነትን በማረጋገጥና ሎጂስቲክስን በማሳደግ እንዲሁም አንድነታቸውን በማጠናከር አህጉራዊ ሰላምን፣ መረጋጋትንና ብልፅግናን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ አስገንዝባለች፡፡ ሁለቱ ሀገራት በተለይም የደቡባዊ ዓለምን የጋራ ጥቅም ለማስጠበቅ በተባበሩት መንግሥታትና እንደ ብሪክስ ባሉ መድረኮች በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በሀገራት መካከል ያለው ግንኙት ስትራቴጂካዊ ነው ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ኢትዮጵያና ቻይና ካላቸው ግንኑነት አንጻር እንዴት ይታያል? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስቶ ምላሽ መስጠት ተገቢ ይሆናል፡፡ ለዚህም ምላሽ ፍለጋ በኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት ዙሪያ ጥልቅ ጥናትና ምርምር በማድረግ የሚታወቁት አሜሪካዊት ምሁር ፕሮፌሰር ዴቦራ ብራውቲጋምን በዋቢነት እንጥቀስ። ፕሮፌሰሯ በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት አስመልክተው የሚሰጡት ትንታኔ፤ ግንኙነቱ ከረድኤት ሰጪና ተቀባይነት ባለፈ ወደ ልማታዊ አጋርነት መሸጋገሩን የሚያረጋግጥ ነው።
ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ተመራማሪዋ ፕሮፌሰር ዴቦራ ብራውቲጋም በገለጻቸው፣ የሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ ትስስር ልዩ የሚያደርገው ቻይና የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ የልማት ፍላጎቶች (እንደ ኢንዱስትሪያላይዜሽንና የመሠረተ ልማት ግንባታ) ከራሷ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ጋር ማቀናጀቷ ነው።

ፕሮፌሰሯ ይህንን አጋርነት የመዋቅር ለውጥ አጋዥ (Structural Transformation Partner) በማለት የሚገልጹት ሲሆን፣ ቻይና በምዕራባውያን ዘንድ እንደሚታየው በፖለቲካዊ ቅድመ-ሁኔታዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ በኢኮኖሚ አቅም ግንባታ ላይ የምታደርገው ትኩረት አጋርነቱ በሁኔታዎች የማይለዋወጥና በጽኑ መሠረት ላይ የቆመ እንዲሆን ማድረጉን በምርምራቸው ያሳያሉ። ግንኙነቱ ስትራቴጂካዊ ነው ሲባልም ትብብሩ በአንድ ዘርፍ የተገደበ ሳይሆን፣ በቴክኖሎጂ፣ በባህል፣ በወታደራዊ፣ በትምህርትና በጤና ዘርፎች ሁሉ የተሳሰረ መሆኑን ያመላክታል።
መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው ‘ዴቨሎፕመንት ሪ ኢማጂንድ’ የተሰኘው ተቋም የልማት ፋይናንስ አማካሪ የሆኑት እፀህይወት ነጋሽ በጉዳዩ ላይ ለቻይናው ሲጂቲኤን በሰጡት አስተያየት ከቻይና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) በብዛት ከሚቀበሉ ስድስት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ስትሆን፤ ከቻይና ጋር ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ መጠን ካላቸው ሀገራትም ትመደባለች። አማካሪዋ አክለውም በኢኮኖሚው ረገድ ያሉ ቁጥሮቹን በአስረጅነት የጠቀሱ ሲሆን እ.ኤ.አ ከ2006 እስከ 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በመሆን 70 ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማከሄዷን በመጥቀስ ግንኙነቱ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ትርጉም ያለው የሁለትዮሽ ትብብር ምን እንደሚመስል ጥሩ ማሳያ ሆኗል ብለዋል፡፡
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉአለም ኃይለማርያም ኢትዮጵያ እንደ ቻይና፣ ህንድና መሰል ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መተባበር እና አንዱ በሌላው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚለው መርህ ሲሆን፣ ይህም ትብብሩን ፍሬያማና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ።
ኢትዮጵያ እንደ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) ያሉ ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ እና የአፍሪካ ህብረት መገኛ እንደመሆኗ በብዙ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ለቻይና ስትራቴጂካዊ አጋር ናት። መምህር ሙሉአለም እንደሚገልፁትም፣ እነዚህ ሀገራት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉት ድጋፍ በዋናነት በመሠረተ ልማትና በኢንዱስትሪ ግንባታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ለዘላቂ ልማት ዋስትና እንደሚሰጥ ጠቁመው፣ ይህ ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት ወደፊትም በጠንካራ መሠረት ላይ ተገንብቶ እንደሚቀጥልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በተለይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ እና ሌሶቶን የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም ቻይና ለአፍሪካ ቀንድና ለቀሪው የአፍሪካ ሀገራት የምትሰጠውን ትኩረት ከማመላከት ባሻገር የኢትዮጵያ-ቻይና ግንኙነት ለአፍሪካ-እስያ ትብብር የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ እንዲቀጥል የጎላ ድርሻ አለው፡፡
የቻይናው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በተለይ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ስልታዊ የኢኮኖሚ ትብብር አጋርነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረውና በቤጂንግ በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (FOCAC) የተመዘገቡ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ