በወንዞች ላይ ነፍስ የዘራው ልማት

You are currently viewing በወንዞች ላይ ነፍስ የዘራው ልማት

“የወንዝ ዳርቻ ልማቱ የአዲስ አበባን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ይጨምረዋል”
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

በዓለም ታሪክ ውስጥ ታላላቅ ስልጣኔዎች የተመሰረቱት በወንዞች ዳርቻ ነው። ወንዞች ለትራንስፖርት፣ ለግብርና እና ለንግድ ስራ መነሻ በመሆናቸው የከተሞች የጀርባ አጥንት ናቸው። በኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት ወንዞች ለፋብሪካዎች ግብዓትና ለቆሻሻ ማስወገጃነት በመዋላቸው ተበክለው ቆይተዋል። ሆኖም ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ እንደ የለንደኗ ቴምዝ፣ የፓሪሷ ሴይን እና የደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል ያሉ ከተሞች ወንዞቻቸውን ወደ መዝናኛ እና የኢኮኖሚ ማዕከልነት በመቀየር ለውጥ አምጥተዋል።

ወንዞችን ማልማት ከመዋብ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት፤ የወንዞችን መበከል ይከላከላል፣ የጎርፍ አደጋን ይቀንሳል፣ የከተማዋን የሙቀት መጠን ያቀዘቅዛል፣ ነዋሪዎች ንጹህ አየር የሚያገኙበትን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበትን እና አዕምሮአቸውን የሚያድሱበትን ዕድል ይፈጥራል። ቱሪስቶችን በመሳብ፣ የንግድ ስራዎችን በማስፋፋት እና የአካባቢውን የመሬትና የቤት ዋጋ ከፍ በማድረግ ረገድም ከፍተኛ ሚና እንዳለው ወንዞቻቸውን በቅጡ አልምተው ወደ ጥቅም ያስገቡ ከተሞች ተሞክሮ ያመላክታል፡፡

የወንዝ ዳርቻቸውን አልምተው የከተሞቻቸውን ገጽታ የቀየሩ ሀገራት መካከል ደቡብ ኮሪያ አንዷ ነች፤ ሀገሪቷ በሴኡል እምብርት በሚገኘው ቼንግጊቼዮን በተባለ ወንዝ የሰራችው ስራ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የቼንግጊቼዮን የወንዝ ልማት ወንዙን ከሞት ማስነሳት ብቻ ሳይሆን በከተማዋ ጥቅጥቅ ባለው የአረንጓዴ አካባቢ አማካኝነት የከተማዋን ሥነ-ምህዳራዊ የደም ቧንቧ እንደገና አቋቁሟል ይባልለታል።

እ.ኤ.አ ከ2003 እስከ 2008 መካከል በተሰራው ስራ አጠቃላይ የብዝሃ ህይወት በ639 በመቶ ጨምሯል። በዚህም በወንዙ ዙሪያ የዕፅዋት ዝርያዎች አይነት ከ62 ወደ 308 ሲያድግ፣ የዓሣ ዝርያዎች ከ4 ወደ 25፣ የወፍ ዝርያዎች እንደዚሁ ከ6 ወደ 36 ከፍ ብሏል። 120 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 100 ሄክታር የሸፈነ አስደናቂ የአካባቢ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን አስገኝቷል፡፡

በተለይም በኢኮኖሚው ረገድ በወንዙ አቅራቢያ ባሉ የመሬት እሴቶች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ አነሳስቶ የቼንግጊቼዮን አካባቢን አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አሳድጓል። ለዚህም ሁለት ማሳያዎችን እናንሳ፤ አንደኛው ስራው በተጠናቀቀ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ በቼንግጊቼዮን አካባቢ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በ3 ነጥብ 5 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ በሌላም በኩል በወንዝ ዳርቻ ልማቱ ዙሪያ 50 ሜትር ርቀት ውስጥ የሚገኙ ንብረቶች የመሬት ዋጋቸው ከልማቱ በኋላ ከ30 እስከ 50 በመቶ ጨምሯል ይላል በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት በደቡብ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰሩ አሌክሳንደር ሮቢንሰን ጥናታዊ ፅሑፍ፡፡

ፕሮፌሰር አሌክሳንደር በጥናት አረጋግጬዋለሁ ባሉት መሰረት የወንዝ ልማት ስራው በየቀኑ በአማካይ 64 ሺህ ጎብኝዎችን የሚስብ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 408ቱ ደግሞ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ናቸው፡፡ በዚህም በሴኡል ከተማ ኢኮኖሚ ላይ የውጪ ጎብኚዎች እስከ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ድረስ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው አስችሏል። በጥቅሉም ወንዙን ወደቀደመ ማንነቱ የመመለስ ስራው ዘላቂ የከተማ መልሶ ማልማት ምልክት ሆኖ በመቆሙም የስነ-ምህዳራዊ መርሆችን ከከተሞች መሠረተ ልማት ጋር በማቀናጀት ከተሞችን እንዴት እንደሚያነቃቁ ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማም ‘ሸገርን ማስዋብ’ በሚባለው ፕሮጀክት የሚከናወኑ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የከተማዋን ወንዞች ገፅታ በመቀየር ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ስራዎች አያሌ ፋይዳዎች አሏቸው፤ ለአብነትም አዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻ እና ለነዋሪዎቿም የምትመች አረንጓዴ ከተማ በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ይጨምራል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በከተማዋ እየተከናወኑ ከሚገኙ ስምንት የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል የቀበና እና የግንፍሌ ወንዞችን የሥራ ሂደት በስፍራው ተገኝተው ገምግመዋል፡፡

የስራ ሂደት ግምገማውን አስመልክቶ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “በእርግጥ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለሀገራችን አዲስ ተሞክሮ ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ አስደናቂና ለውጥ አምጪ ሥራዎች ተከናውነዋል። በተለይም 19 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና ከእንጦጦ እስከ ካራማራ ድልድይ ድረስ የሚዘልቀው የቀበና ፕሮጀክት፣ ልክ እንደ እንጦጦና ፒኮክ ፓርኮች ሁሉ በአሁኑ ወቅት ግንባታው ወደ መጠናቀቂያው ተቃርቧል” ብለዋል።

ብክለት ተወግዶ፣ የአፈርና የሥነ-ምህዳር ጥበቃ ተደርጎላቸው፣ ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን አጥተው የነበሩ ወንዞቻችን ታክመው ሲያንሰራሩ ማየት ትልቅ ስኬት ነው ያሉት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ የደረቁ የውሃ ምንጮች እንደገና ሲፈልቁ፣ መጥፎ ሽታ ተወግዶ አካባቢው በሀገር በቀል ዛፎች ተከብቦ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ጤናማና ንጹሕ አየር የሚተነፈስበት ማራኪ ገጽታ ሲላበስ ማየት የልፋታችን ትልቁ ውጤት ነው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አክለውም፣ “የከተማችንን ዘላቂ ልማት የሚያረጋግጡ የውሃ ግድቦች፣ በርካታ ድልድዮች፣ ቼክ ዳሞች፣ ዘመናዊ የእግረኛና የሳይክል መንገዶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የልጆች መጫወቻዎች፣ ካፌና ሬስቶራንቶች እንዲሁም ሰፋፊ የመኪና ማቆሚያዎች ተገንብተዋል። የከተማችንን ገጽታ የሚቀይሩ የአረንጓዴና የውበት ሥራዎችም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ”ም ብለዋል፡፡

ይህ ልማት በአሁኑ ወቅት ለሪል እስቴትና ለሆቴል አልሚዎች እጅግ አዋጭ የኢንቨስትመንት አካባቢ ፈጥሯል በማለት፣ ዕውቀትና ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶች በዚህ ልዩ የልማት ዕድል ላይ እንደወትሮው በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህንን ፕሮጀክት ከውጥን እስከ ፍጻሜው እውን ለማድረግ ሌት ተቀን ለደከሙ አመራሮች፣ ኮንትራክተሮች፣ ባለሙያዎች፣ ኢንተርፕራይዞችና የልማቱ ባለቤት ለሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከእንጦጦ ተራሮች ተነስተው በከተማዋ በኩል አልፈው አቃቂ ወንዝ ድረስ በሚጓዙ ትልልቅ ወንዞች ላይ የተጀመረው የወንዝ ዳርቻ ልማት ለከተማዋ ነዋሪዎች የዓመታት ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ስለመሆናቸው መናገር ይቻላል፡፡

ከእንጦጦ ተራራ በጉለሌ በኩል አፍሪካ ህብረት እንዲሁም ከእንጦጦ በአፍንጮ በር በባንቢስ አድርጎ አቃቂ የውሃ ማጣሪያን በሚሸፍነው ፕሮጀክት በውስጡ 28 የሚደርሱ ድልድዮች፣ ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ አረንጓዴ ቦታዎች፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የውኃ ትራንስፖርት እና የንግድ ማዕከላት ይገነቡበታል። ልማቱ ለእግር ጉዞና የመሮጫ ትራኮች፣ የብስክሌት መስመሮች፣ ኬብል ካር ትራንስፖርት (የገመድ ላይ መኪና)፣ መዝናኛ ግድቦችን ይዟል፡፡

ፕሮጀክቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ደህንነት በማሻሻልና የከተማዋን እይታ ይበልጥ በመለወጥ ረገድ ብዙ ሚና ከመጫወቱ በተጨማሪ የተለያዩ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች እንዲሁም ለጎብኚዎች የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ስፍራዎችን በማዘጋጀት የውጪ ሀገርና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ አዲስ አበባ መሳብ ያስችላል ተብሎለታል፡፡ ለከተማዋ ነዋሪ ተጨማሪ ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር፤ በወንዞች ዳርቻ እና ህዝብ በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች የአገልግሎት ዘርፉን በማበረታታት ካፌዎች፣ ምግብ ቤቶች፣ የከተማ አስጎብኚዎችና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ማመቻቸት፤ የተፋሰስ ወንዞች ዳርቻ እና የፕሮጀክቱ ዳርቻ ያሉና ወደፊት የሚገነቡ የሪልስቴት ፕሮጀክቶችም የዕቅዱ አካል ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ስራዎች ታዲያ ለመዲናዋ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጉልበት እንደሚሰጡ መረዳት ይቻላል።

የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማዋን ገጽታ በመቀየር እና ወደ ዘመናዊ ከተሜነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ ቦታ ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡ በኢኮኖሚው እና በማህበራዊው ዘርፍ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ልማቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም የአዲስ አበባን ኢኮኖሚ እና የነዋሪዎቿን ኑሮ ደረጃ ከፍ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

አሲሲዮና ገጸ ድር ወንዞችን አስመልክቶ ያወጣው መረጃም የሚያጠናክረው እውነት ወንዞችን ማልማት ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አለመሆኑን ነው። በዓለም ላይ ከ2 ቢሊዮን በላይ ሰዎች በቀጥታ በወንዞች ላይ በመጠጥ ውሃ ጥገኛ ሲሆኑ፣ 25 በመቶ የዓለም የምግብ ምርት የሚቀርበውም ከወንዞች በሚገኝ ውሃ ነው። እንደዚሁም በዓመት ቢያንስ 12 ሚሊዮን ቶን ዓሳ የሚገኘው ከዚሁ ከወንዝ ነው ይላል የገጸ ድሩ መረጃ፡፡

ወንዞች በአካባቢ ጥበቃ፣ ለተፈጥሮ ሚዛን ማስጠበቂያ፣ መዝናኛ እንደዚሁም ለሰው ልጆች እድገት ያላቸው አበርክቶ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይሁንና አዲስ አበባ ለዓመታት በጉያዋ ያቀፈቻቸው ወደ 600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑት ወንዞች ግን ለዚህ አልታደሉም ነበር፡፡ በመዲናዋ የሚገኙት እነዚህ ወንዞች ፍሰታቸው ወቅታዊና ተለዋዋጭ ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ ደረቅ ናቸው፡፡ ለዘመናት ለቀማኛ መደበቂያ፣ የመጥፎ ሽታ መገለጫ፣ የሞቱ እንሰሳት መጣያ ሆነው ቆይተዋል፡፡ በሌላም በኩል በርካታ የጥናት ውጤቶች እንደሚያመለክቱትም የመዲናዋ ወንዞች ከመኖሪያ መንደሮች በሚወጡ ውጋጆችና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች በተረፈ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ የተበከሉ ነበሩ፡፡ አሁን ግን በወንዞች ዳርቻ ልማት አማካኝነት ገፅታቸው እየተቀየረ ውብ እና ሳቢ መልክም እየተላበሱ ይገኛሉ፡፡

በአጠቃላይ፣ የወንዞች ልማት የአዲስ አበባን የከተማ ገፅታ በማሳመር፣ ኢንቨስትመንትንና ቱሪዝምን በመሳብ፣ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ እና በጤና ላይ የሚወጣን ወጪ በመቀነስ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው። የወንዝ ዳርቻ ልማት ለአዲስ አበባ ከተማ ከተሜነትን፣ ውበትን፣ ጽዳትን እና የኢኮኖሚ ጥንካሬን በማምጣት ተወዳዳሪ እና ለኑሮ ምቹ የሆነች ከተማ እንድትሆን የሚያደርግ አስኳል ፕሮጀክት ነው ማለት ይቻላል።

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review