የበጎነት አቅም

You are currently viewing የበጎነት አቅም

“ደም መለገስ ምንም ሳንከፍል ከተሰጠን ከፍለን፤ ሌሎችን ለማዳን የምናደርገው በጎነት ነው”
ለ27ኛ ጊዜ ደም የለገሱት ዶክተር አብርሃም መክብብ
“ከፈራረሰ ቤት ወጥቼ ንጹህ ቤት ውስጥ በመግባቴ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል
ቤት የታደሰላቸው ወ/ሮ ታደለች ቱሉ

“በአንድ የጤና ተቋም ምሽት ተረኛ ሆኜ እየሰራሁ ነበር፡፡ በስለት ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ህክምና ተቋማችን የመጡትን አንዲት እናት ህይወት ለማዳን ቀዶ ህክምና ማድረግ ያስፈልግ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ የመጣች ወጣት የደም መጠኗ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ነበር። በወቅቱ የሁለቱን ሴቶች ህይወት ለማዳን ከሚያስፈልገው ደም ለአንዷ ከሆስፒታሉ ስናገኝ፤ ለሁለተኛዋ አላገኘንም ነበር። በዚህ ምክንያትም የአንዷን ታካሚ ህይወት አጣን፡፡” ይላሉ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ጤና ጣቢያ ጠቅላላ ሀኪም የሆኑት እና በክፍለ ከተማ በተዘጋጀ የደም ልገሳ መርሀ ግብር ላይ ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው ዶክተር አብርሃም መክብብ፡፡

በወቅቱ በደም እጦት ምክንያት የሰው ህይወት ሲያልፍ ማየታቸው፤ የአስረኛ ክፍል ተማሪ ሆነው የጀመሩትን ደም የመለገስ የበጎ ፈቃድ ተግባር እንደ ልምድ አድርገው እንዲገፉበት ምክንያት እንደሆናቸው ዶክተር አብርሃም ይናገራሉ፡፡ እስከአሁን ድረስ ለ27 ጊዜ ደም ለግሰዋል፡፡

“የህክምና ባለሙያ ነኝ፤ ደም መለገስ በጤና ላይ የሚያስከትለው ምንም ጉዳት የለም፤ በተቃራኒው የብዙ ሰዎችን ሕይወት ይታደጋል፡፡ ደም መለገስ ደስ ያሰኛል፤ እርካታም አለው፡፡ ደም ስለግስ የሆነ ሰውን ህይወት አድኛለሁ ማለት ነው፡፡” ሲሉም የሚሰማቸውን ስሜት አብራርተዋል፡፡ 

በተለይ በልገሳ ፕላትሌት የሚባለው የደም ተዋፅኦ እንደተፈለገ የማይገኝ እንደሆነ የሚያነሱት በጎ ፈቃደኛው የህክምና ባለሙያ፣ “ራሴ የምከታተለው የፕላትሌት የደም ተዋፅኦው ዝቅተኛ የሆነ ታካሚ ነበረኝ፡፡ እኔ ደም ስለግስ የዚህ ሰው ህይወት ይድናል ማለት ነው። ደም መለገስ ምንም ሳንከፍል ከተሰጠን ከፍለን፤ ሌሎችን ለማዳን የምናደርገው በጎነት ነው” ይላሉ፡፡

በጎነት ዓይነቱ፣ ፋይዳውና መገለጫው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በጎ አድራጊዎች በሚያደርጉት የበጎነት ተግባር የበርካቶችን ህይወት መታደግ፣ የዘመሙ ጎጆዎችን ማቃናት፣ ጠያቂ የሌላቸው እናቶች፣ አባቶች፣ የሀገር ባለውለታዎችን እንባ ማበስ ተችሏል፡፡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቤት እድሳት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ ታደለች ቱሉ አንዷ ናቸው። ወይዘሮ ታደለች  በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ ወይራ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከ50 ዓመታት በላይም በአካባቢው ኖረዋል፡፡ ከወላጆቻቸው ባገኙት ቤት ከእህትና ወንድሞቻቸው ጋር አምስት ሆነው በአንድ ቤት አብረው እየኖሩ ይገኛሉ፡፡

ወይዘሮ ታደለች በአንድ የግል ድርጅት በትራንዚት ባለሙያነት ተቀጥረው እየሰሩ በሚያገኙት ገቢ ነበር ህይወታቸውን የሚመሩት፡፡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ስራው ሲቆም ቤት ውስጥ ለመቀመጥ እንደተገደዱና ሲገኝ እንጀራ በመጋገር እና የተገኘውን በመስራት ህይወታቸውን እየመሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡

የሚኖሩበት ቤት በእንጨት፣ ጭቃና ቆርቆሮ የተሰራ ሲሆን ለረጅም ዓመት ሳይታደስ በመቆየቱ ግርግዳው ፈራርሶና ዘምሞ ነበር፡፡ በተለይ የክረምት ወቅት ሲመጣ፣ ዝናብ ሲዘንብ ከላይ የጣሪያው ቆርቆሮ በጊዜ ብዛት በማርጀቱና በመበሳሳቱ የተነሳ ከዝናብ የሚያስጥል አልነበረም፡፡ ከታችም ጎርፍ ወደ ቤታቸው እየገባ ዕቃቸውን ያበላሽባቸው ነበር፡፡

ሌላኛዋ የወይዘሮ ታደለች እህትና የቤተሰቡ አባል ወይዘሮ ሾላዬ ቱሉ እንዲሁ ቤታቸው እንደቤት ከዝናብና ቁር የሚታደጋቸው፣ እረፍት አድርገው በሰላምና ምቾት የሚኖሩበት እንዳልነበረ ይናገራሉ፡፡ “ቤታችን ለረጅም ጊዜ ያለእድሳት በመቆየቱ ከኋላ ያለው ግድግድ መፍረስ ጀምሮ ነበር፡፡ በተለይ በክረምት ወቅት ከላይ የሚዘንበው ዝናብ ጣሪያው ስለሚያፈስ  እቃ እየደቀንን ውሃን ለመያዝ እንሞክር ነበር፡፡ ከመሬት ስርም ጎርፍ እየገባ ቤታችንን በውሃ ይሞላል። አንዳንድ ጊዜ ጎረቤቶቻችን እየመጡ የገባውን ውሃ በማስወጣትና ቤቱን በማፅዳት ያግዙን ነበር፡፡ ቤታቸውም እየሄድን እናድር ነበር” በማለት ያለፉትን ፈተና ያስረዳሉ፡፡

ወይዘሮ ታደለች የዘመመው ጎጇቸውን ለማሳደስ ፍላጎት ቢኖራቸውም አቅማቸው ግን ይህንን የሚፈቅድ አልነበረም። በዚህ ምክንያትም በተለያዩ ጊዜያት ቤቱ እንዲታደስላቸው ለሚኖሩበት የወረዳ አስተዳደር ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ እህታቸው ወይዘሮ ሾላዬ የሚያገኙት ገቢ ከእጅ ወደ አፍ የሚባል በመሆኑ በራሳቸው ለማሳደስ አቅም እንደሚያንሳቸው ያነሳሉ፡፡ የልብስ ስፌት ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ ቆይተው በጤና እክል ምክንያት ስራውን መቀጠል ስላልቻሉ በአሁኑ ወቅት በአንድ የጤና ተቋም በሚገኝ ክበብ በመስተንግዶ ተቀጥረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ሌሎች የቤተሰብ አባላትም ቢሆን የሚያገኙት ገቢ የቤት ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ የሚተርፍ እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡

እነሆ ጊዜው ደርሶ የወይዘሮ ታደለች ቤት በልበ ቀና በጎ አድራጊዎች ድጋፍ አማካኝነት ፈርሶ፣ በእንጨትና ጭቃ ተሰርቶ የነበረው በብሎኬት ተገንብቶ፣ ቀለም ተቀብቶ ውብና ንፁህ ሆኖ ይገኛል፡፡ “ከፈራረሰ፣ ከሚያፈስ ቤት ወጥቼ፣ ንጹህ እና በደንብ የተሰራ ቤት ውስጥ በመግባቴ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በሰላም ውለን ወደ ቤት እየገባን ነው፡፡ አሁን እንደበፊቱ ዕቃችንና መኝታ ቤታችን አይበላሽም፤ ቤታችን በፊት የነበረውን የሚያውቀው ሁሉ በምን ዓይነት ንፁህ ቤት ውስጥ እየኖርን እንደሆነ ይመሰክራል፡፡” ሲሉ የተሰማቸውን ደስታ ይናገራሉ፡፡ 

ወይዘሮዋ በማብራሪያቸው፤ “ከምስጋና በላይ የማቀርበው ነገር የለም፤ እግዚአብሔር ውለታቸውን ይክፈላቸው፤ ድሃን እንዲህ ወርዶ ማየቱ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ይህ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ኢትዮጵያውያንም እየተደረገ ነው” ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ፋንታዬ ታደለ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡ በወረዳው የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፤ እየተሰሩም ይገኛል፡፡ የአቅመ ደካሞችን፣ የሀገር ባለውለታዎችንና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን ቤት በማደስ፣ ደም በመለገስ፣ ማዕድ በማጋራት፣ ነፃ የትምህርት እና ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

ከሐምሌ 2017 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በወረዳው ባለሀብቶችንና በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ ያሉ የጤና፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ሌሎች የዘርፍ ጽህፈት ቤቶችን በማስተባበር 18 የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ ተችሏል፡፡ ከዚህ ባሻገር ደም በመለገስ፣ በበጎነት በሆስፒታል እና በሆስፒታል አካባቢ ህሙማንን በመጠየቅና በሌሎች ዘርፎች የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ለማከናወን መታቀዱን ወይዘሮ ፋንታዬ አብራርተዋል፡፡

እንደ ከተማ ምን እየተሰራ ነው?

በአዲስ አበባ ከተማ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ እንዲሁም ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ብሎም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የበጎ ፈቃድ ግንዛቤ ማስረፅ ቡድን መሪ አቶ ቢኒያም ጊቻ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ ዜጎች  በግልም ሆነ በተደራጀ መንገድ በበጎ ፈቃደኝነት በመሳተፍ ጊዜያቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ለወገናቸው ማዋል እንደቻሉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡

የ2018 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ጥቅምት 20 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን እስከ ግንቦት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይቆያል፡፡ ከ500 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች በ13 ዋና ዋና መርሀ ግብሮች  እና 12 ንዑስ መርሀ ግብሮች ላይ በድግግሞሽ ይሳተፋሉ፡፡ በዚህም 911 ሺህ 200 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ በዚህም ይወጣ የነበረን 9 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የመንግስት ወጪን ለማዳን መታቀዱን አቶ ቢኒያም ተናግረዋል፡፡

በበጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል የቤት ግንባታ መርሃ ግብር አንዱ ሲሆን፣ 1 ሺህ 900 ቤቶችን በመገንባት 9 ሺህ 500 አረጋዊያን፣ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የሀገር ባለውለታዎች እንዲሁም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም 25 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ይሳተፋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም እነዚህን ስራዎች ለማከናወን ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ መገባቱን አቶ ቢኒያም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፣ በደም ልገሳ መርሃ ግብር በበጋው የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር 32 ሺህ 600 በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ 32 ሺህ 600 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥም 8 ሺህ 977 ዩኒት ደም ማሰባሰብ ተችሏል፡፡

“አንድ ሰው ለአንድ ቤተሰብ” በተሰኘው መርሃ ግብር ከተለያዩ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር በበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 29 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ቢያንስ ለሶስት ወራትና ከዚያ በላይ በሚዘልቅ ጊዜ ማዕድ በማጋራት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራትም 3 ሺህ 712 ቤተሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አክለዋል፡፡

በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት 4 ሺህ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ ለተገልጋዮች መረጃ ከመስጠት ጀምሮ በተለያየ መልኩ በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራትም 1 ሺህ 388 በጎ ፈቃደኞችን ማሳተፍ እንደተቻለ አቶ ቢኒያም ገልጸዋል፡፡

በሙያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፕሮግራም በበጋው ወራት 3 ሺህ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ መምህራን፣ የህክምና፣ የኪነ ጥበብና የህግ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለሙያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን ባለፉት ሁለት ወራት 913 በጎ ፈቃደኞችን ማሰማራት ተችሏል፡፡

በጎነት በሆስፒታል፣ በመንገድ ትራፊክ አገልግሎት፣ በሰላም እሴት ግንባታ፣ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ ማዋል፣ የአደጋ ጊዜ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና ሌሎች  መርሃ ግብሮች በርካታ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል እየተሰራ እንደሚገኝም ቡድን መሪው ገልጸዋል፡፡

በጎ ፈቃድ ባህል እንዲሆን መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም፣ መድረኮችን፣ የፓናል ውይይቶችን በማዘጋጀት፣ የተሰሩ ስራዎችን በማስተዋወቅ፣ ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃድ ቀንን በማክበርና የተለያዩ ኹነቶችን በመጠቀም እየተሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር ቀደም ብሎ የፀደቀውና ባለፈው ዓመት ተግባራዊ መሆን የጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የማህበራዊ ኃላፊነት አሰራር ደንብ ቁጥር 161/2016ን በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ስራ ለማስገባት፣ ዜጎች በግልና በተደራጀ መንገድ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል በደንቡ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ ግንዛቤ ማስረፅ ቡድን መሪው አቶ ቢኒያም እንደሚያብራሩት፣ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአዲስ አበባ በጎ ፈቃደኝነት ተቋማዊ እንዲሆን ተደርጎ በመሰራቱ በርካታ ውጤቶችን ማምጣት ተችሏል፡፡

ከ2011 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ባሉት ሰባት ዓመታት ከ15 በላይ ዋና ዋና አሳታፊ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሮችን በመቅረፅና በጎ ፈቃደኞችን ባሳተፈ መልኩ በመሰራቱ የበጎ ፈቃድ ባህልና ተደራሽነቱ እንዲያድግ ማድረግ ተችሏል። የቤት ግንባታ መርሃ ግብርን ብናነሳ  ባለፉት ሰባት ዓመታት 40 ሺህ 576 ቤቶች በአዲስ መልክ ተገንብተውና ታድሰው ለአቅመ ደካሞች፣ አረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለሀገር ባለውለታዎች ተላልፈዋል፡፡ በዚህ ተግባር 173 ሺህ 530 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ይህ የቤት ግንባታ በወቅቱ በነበረው የገበያ ሁኔታ በገንዘብ ሲተመን ከ19 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው እንደሆነ አቶ ቢኒያም ጠቁመዋል፡፡

በማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ደግሞ በድግግሞሽ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በአማካይ በየዓመቱ ከ700 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ ማጋራት የተቻለ ሲሆን፤ በገንዘብ ሲተመን ከ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ አለው፡፡ በደም ልገሳ መርሃ ግብር 309 ሺህ 102 ዩኒት ደም በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር ማሰባሰብ ተችሏል፡፡ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት አገልግሎት ፕሮግራም፤ በተመረጡ አደባባዮች 40 ሺህ 660 በጎ ፈቃደኞች ተሰማርተው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል። በነጻ ህክምና፣ በህፃናት ድጋፍ፣ በወሰን የለሽ እና ሌሎች ፕሮግራሞች በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አቶ ቢኒያም አብራርተዋል፡፡

በጥቅሉ በአዲስ አበባ በበጎ ፈቃደኞች የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ከተማዋን በአገልግሎቱ ተምሳሌት እንድትሆን አድርጓታል፡፡ በበጎ ፈቃድ ስራዎች የበርካታ ነዋሪዎችን ህይወት ማቃለልና ማቃናት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መፍታት ተችሏል፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አሁን ካለው የበለጠ ለማስፋትና በጎነት ባህል እንዲሆን ከመንግስት ባሻገር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል እንላለን፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review