የስማርት ወረዳዎች አገልግሎት አሰጣጥምን ውጤት አመጣ?

You are currently viewing የስማርት ወረዳዎች አገልግሎት አሰጣጥምን ውጤት አመጣ?

በመዲናችን አዲስ አበባ አገልግሎት አሰጣጡን የተቀላጠፈና ዘመናዊ ለማድረግ  ተቋማትን የማዘመን ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ከነዚህ መካከል ስማርት የወረዳ አስተዳደር ህንጻዎች ግንባታ ተጠቃሽ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳን ሶስት ዘመናዊ ባለ10 ወለል የወረዳ አስተዳደር ህንጻዎች ተገንብተው ወደ አገልግሎት መግባታችው ይታወቃል። ለመሆኑ እነዚህ ህንጻዎች ለአገልጋዮች እና ተገልጋዮች ምቹ ከባቢን በመፍጠር አገልግሎቱን ከማሳለጥ አንጻር ያላቸው አበርክቶ እንዴት ያለ ነው? የሚለውን ለመዳሰስ ወደድን፡፡

ወይዘሮ ራህመት ዲኖን ያገኘናቸው ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ከበቁት መካከል  በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 አስተዳደር ቅኝት ባደረግንበት ወቅት መታወቂያ ሲያሳድሱ ነው፡፡ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ “ከዚህ በፊት የግብር  ከፋይ መለያ ቁጥር ለማውጣት ወረፋ፣  ከአንዱ ቢሮ ወደ ሌላኛው ቢሮ  መንከራተት እንዲሁም ይህን ስላላሟላሽ ለነገ እያሉ ጊዜና ጉልበታችን ይባክናል፣ ለአላስፈላጊ የትራንስፖርት ወጪም እንዳረግ ነበር” ሲሉ ከዚህ በፊት የነበረውን እንግልት ነግረውናል፡፡ 

“አሁን ላይ በወረዳው የሚሰጠው አገልግሎት በቴክኖሎጂ የታገዘ በኦን ላይን በመሆኑ መታወቂያዬን 5 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዳድስ አድርጎኛል፡፡ ይህም የሆነው አገልግሎት ሰጭዎቹ ሲስተሙ የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ይሞሉልናል። ከእኛ የሚጠበቀው መረጃ አሟልቶ መገኘት ብቻ ነው፡፡ ይህ የሆነው የወረዳ አስተዳደሩ ህንጻ ዘመናዊ ሆኖ በመገንባቱ ነው” ሲሉ አሁን ላይ ጥሩ የሆነ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ሌላኛው በወረዳው ለወንድማቸው በውክልና የንግድ ፈቃድ ሊያሳድሱ መጥተው ያገኘናቸው አቶ አብዱልቃድር በድሩ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረውን አገልግሎት አሰጣጥ የገለጹት “ኋላ ቀር” በሚል ነበር፡፡ “ከዚህ በፊት ለአገልግሎት 102 ብር ከፈልኩ፡፡ ሌላ ጊዜ ስሄድ ሳትከፍል ብዙ ጊዜ አሳልፈሃል በሚል 8 ሺህ በር እንድከፍል ተደርጌያለሁ። ይህ የሆነው አገልግሎቱ የተሰጠበት ወረቀት በመጥፋቱ ነው” ሲሉ በማሳያነት አንስተው አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ አብዱልቃድር ገለጻ፣ የአሁኑ አሰራር  ከእንደዚህ አይነት ችግር የሚገላግል ነው፡፡  እሳቸውም ተገቢውን አገልግሎት በፍጥነት እና በቅልጥፍና ማግኘት ችለዋል፡፡ ወረቀት ይዞ ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል መንከራተትን ቀርቷል፡፡ እያንዳንዱ መረጃ ኮምፒዩተር ላይ ስለተመዘገበ  ይጠፋል የሚል ስጋት የተለም፡፡ 

ወይዘሮ ልደት ወልዴንም በወረዳው የንግድ ፈቃድ ሊያወጡ መጥተው ነው ያገኘናቸው፡፡ የአከራይ ተከራይ ውል ለመዋዋል እንደመጡ ነግረውናል፡፡  አሁን እየተሰጠ ያለው አገልግሎት በኦን ላይን በመሆኑ ያለምንም እንግልት አገልግሎቱን አግኝተዋል፡፡ “ነገ ወይም ከነገ ወዲያ ተመልሰሽ ነይ” በሚባል የሚሰጥ ቀጠሮ እንደሌለም ገልጸዋል፡፡ 

“ከዚህ በፊት ጉዳይ ለማስፈፀም  ግማሽ አልያም ሙሉ ቀን ይወስድ ነበር። አሁን ግን 20 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጨርሻለሁ፡፡ ይህም ጊዜዬን ቆጥቦልኛል፤ ምልልሱንም አስቀርቶልኛል” ብለዋል፡፡ 

በተቋሙ የግብር አወሳሰን ባለሙያ አቶ ቶለሳ ዲባባ በበኩላቸው፣ “አሁን እየሰራን ያለነው ስራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ነው፡፡ ይህም የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ በፊት የአንድን ሰው ስም ለመፈለግ ወረቀት ማገላበጥን ይጠይቅ ነበር፡፡ አሁን ግን የተገልጋዩን ስልክ ቁጥር ወይም የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር በማስገባት የምንፈልገውን መረጃ ቶሎ ማግኘት እንችላለን፡፡” ሲሉ አብርርተዋል፡፡

እንደ ገቢዎች ቢሮ በአጭር የመልክት ማስተላለፊያ ቁጥር 7075 የሚወሰኑ ውሳኔዎችን፣ ግብር መክፈል ሲፈልጉ  ባሉበት ሆነው በስልካቸው እንዲከፍሉ የሚደረግበት መንገድ እንዳለ እና ደረሰኙም በስልካቸው እንዲደርሳቸው ስለሚደረግ አሰራሩ ስራን እንደሚያቀላጥፍ ነው  አቶ ቶለሳ የገለጹት፡፡

“የሰራናቸውን ስራዎች ሪፖርት ለማድረግ ቀላል ነው፡፡ የተመቻቸ የህፃናት ማቆያ፣ መጫወቻ፣ መኪና ማቆሚያ እና ካፍቴሪያ መኖሩ ደግሞ ባለሙያዎች ተረጋግተው እንዲሰሩ ስለሚያደርግ  አገልግሎት አሰጣጡን የተሳለጠ ያደርገዋል” ሲሉም አክለዋል፡፡

አቶ ተክሉ ጋሞ በወረዳው የሲቪል ምዝገባና ነዋሪዎች አገልግሎት ሪከርድና ማህደር ክፍል ቡድን መሪ ናቸው፡፡ አገልግሎቱ በወረቀት በሚሰጥበት ወቅት ተገልጋዮች ይጉላሉ ነበር፡፡ አሰራሩም ለእጅ መንሻ የተጋለጠ ነበር በማለት፣ በአሁኑ ወቅት ግን በሲስተም ስለሚሰራ እንደነዚህ አይነት ችግሮች መቀረፋቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፣ አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ መደገፉ ከተገልጋዮች የሚመጡ ቅሬታዎችን አስቀርቷል፡፡ በወረቀት በሚሰራበት ወቅት የነበረውን እንግልት እና ስህተትም ቀንሷል፡፡ 

በሌላ በኩል  በወረዳው ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው መጥተው የሚያቆዩበት የህፃናት ማቆያ፣ የካፍቴሪያ እንዲሁም የምንፈልገውን ነገር ገዝተን እንድንሄድ የተመቻቸ የሰራተኞች ሱቅ መኖሩ ተረጋግተን ስራችንን እንድንሰራ እና ጊዜያችን ተጠቅመን የተቀላጠፈ አገልግሎት እንድንሰጥ የሚያግዝ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

በልደታ ክፍለ ከተማ የወረዳ 2 ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሃምዛ ከድር በበኩላቸው፤ ወረዳው ከዚህ በፊት አራት የግለሰብ ቤቶችን ተከራይቶ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይቷል፡፡ በ2018 ዓ.ም ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ የስማርት ወረዳ ስታንዳርድን በጠበቀ መልኩ ባስገነባው ህንጻ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡

ህንጻው አካል ጉዳተኞችንና አቅመ ደካሞችን ታሳቢ ያደረጉ ሁለት ሊፍቶች አሉት፡፡ ለሰራተኛው የሚያስፈልጉ የህፃናት ማቆያና መጫወቻ ቦታ፣  ካፍቴሪያ፣ ሰራተኞች የፍጆታ እቃዎች ሲፈልጉ የሚገበዩበት የሸማቾች ሱቅ፣ የመንገድ ጥርጊያ ወይም የፅዳት ሰራተኞች ንፅህናቸውን የሚጠብቁበት መታጠቢያ ቤት፣ ተገልጋዮች መኪናቸውን የሚያቆሙበት የመኪና ማቆሚያ አይነት አገልግሎቶችንም አካትቷል፡፡

ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ ስራዎች እየተሰሩ ያሉት በቴክኖሎጂ ታግዞ መሆኑን የሚገልጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ ይህም ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት በመስጠት የአገልጋዩን የስራ ጫና፣ የተገልጋዮችን እንግልት የቀነሰ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የልደታ ወረዳ 2’ን ማሳያ አደረግን እንጂ ለአገልግሎት አሰጣጡ መዘመን ቁልፍ ሚና ያላቸው የስማርት ወረዳ አስተዳደር ህንጻዎች በሌሎች አካባቢዎችም ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

አቶ በቀለ ተመስገን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአገልግሎት አሰጣጥና አውትሶርሲንግ ዘርፍ ኃላፊ ናቸው፡፡ በከተማዋ  በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማሳለጥና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት እንዲችሉ ተቋማትን ስማርት የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ስማርት ወረዳዎች ሲባል ከህንፃው ግንባታ ጀምሮ አካታች የሆኑ፣ በየተቋሙ ለሚሰሩ ሰራተኞች እንደ ህፃናት ማቆያ፣ የካፍቴሪያ፣ የመኪና ማቆሚያ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮች የተሟሉለት መሆኑን ተናግረዋል

ወረዳዎች ስማርት መሆናቸው አገልግሎት አሰጣጡን ከማቀላጠፍ ባሻገር ተጠያቂነትንም የሚቀንስ ነው። ስማርት ሲባል አገልግሎት አሰጣጡን ወረቀት አልባ በሆነ መንገድ የሚሰራበት መንገድ ነው፡፡ ለዚህም በምሳሌነት አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠቃሽ ነው፡፡ የተሰሩት ስማርት ወረዳዎችም ተገልጋዮች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እንዲሁም ወጭያቸውን በመቀነስ አገልግሎትን በተቀላጠፈ መንገድ እንዲያገኙ፣ አገልጋዮችም ፍጥነት ያለውና የተቀላጠፈ አገልግሎት እዲሰጡ የሚያደርግ ነው፡፡

ተገልጋዮች በአንድ ቦታ ላይ ጉዳያቸውን ጨርሰው የሚመለሱበት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ እስከ አሁን በታዩት ጅምሮች ውጤታማ መሆን ተችሏል። እንዲህ አይነት ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ አቶ በቀለ ተናግረዋል፡፡  

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review