በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል የጥበብ ስራዎች መቅረባቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የመጽሐፍ ውይይት፣ ሙዚቃ፣ የሥዕል አውደ ርዕይ እና የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ጥቂቶችን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጽሐፍት
በዛሬው እለት በእጓለ ገብረ ዮሐንስ በተጻፈው እና “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ መርሃ ግብሩ የሚካሄደው 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን ቦታው ደግሞ ቀበና፣ የካቶሊክ ኪዳነምሕረት ትምህርት ቤት አቅራቢያ፣ ወደ ሳንፎርድ ትምህርት ቤት በሚወስደው መንገድ፣ ባማ አዲስ ሕንፃ አጠገብ፣ FSS አዳራሽ ነው፡፡ የነገረ-መጽሐፍት ዝግጅት አካል የሆነው ይህ የመጽሐፍ ውይይት መርሃ ግብር የተሰናዳው በዛጎል የመጽሐፍት ባንክ ሲሆን፣ ኢዛና አምደወርቅ (ዶ/ር) የመወያያ ሃሳብ ያቀርባል፡፡ አዘጋጁ ደግሞ ታዋቂው ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ( ዶ/ር) ነው፡፡
በሌላ መረጃ “አብሪ ቀለማት – ከቅኔ ቤት እስከ ባሕር ማዶ” የተሰኘ መጽሐፍ ከሰሞኑ ለንባብ በቅቷል፡፡ መጽሐፉ የተጻፈው በታደለ ገድሌ (ዶ/ር) ሲሆን አስተማሪ የህይወት ገጠመኞችና ታሪኮችን የያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የስእል አውደ ርዕይ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምስረታ ክብረበዓልን አስመልክቶ በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የተዘጋጀው የስእል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ ይገኛል፡፡ አውደ ርእዩ የተዘጋጀው በትምህርት ቤቱ የቀድሞ ምሩቃን ነው። ቅዳሜ ጠዋትን ጨምሮ፣ በሥራ ሰዓትና በሥራ ቀናት ለሁሉም ተመልካች ክፍት መሆኑም ተገልጿል፡፡ አውደ ርዕይው እስከ መጪው ጥር 22 በእይታ ላይ ይቆያል፡፡
የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ
ከታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲታይ የነበረው የአብነት ተሾመ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ ነገ ይጠናቀቃል፡፡ “ሪፍሬም ኢትዮጵያ” (ኢትዮጵያ ከሌላ ማእዘን) በሚል ርእስ በተዘጋጀው በዚህ አውደ ርዕይ የኢትዮጵያን ተፈጥሮ፣ ባህል፣ ማንነትና አኗኗር የሚያሳዩ በርካታ ፎቶ ግራፎች ለእይታ ቀርበውበታል፡፡ አውደ ርዕዩ እየታየ የሚገኘው በአርታዊ ጋለሪ ሲሆን ከዮድ አቢሲኒያ 250 ሜትር ገባ ብሎ ነው፡፡
ሙዚቃ
ድምጻዊት ያለምወርቅ ጀምበሩ አዲስ የሙዚቃ ስራ ለአድማጭ ተመልካች ይፋ ልታደርግ ነው፡፡ “ምንትዋብ” የተሰኘው ይህ ስራ ዛሬ ማታ በናሆም ሪከርድስ አማካኝነት እንደሚለቀቅ ተሰምቷል። ድምጻዊት ያለምወርቅ ጀምበሩ ከዚህ ቀደም ማለትም በ3ኛው የፋና ላምሮት የሙዘቃ ውድድር የአሸናፊዎች አሸናፊ የነበረች ሲሆን የክቴ፣ ምነው፣ ኢትዮጵያ ታየችኝ፣ እርሺው አሉኝና ሌሎችንም የሙዚቃ ስራዎች ወደ ህዝብ አድርሳለች።
በሌላ መረጃ የቴድሮስ ታለ አዲስ የሙዚቃ አልበም በዛሬው እለት ይለቀቃል፡፡ “አይመጥንም” የተሰኘው የሙዚቃ አልበም በድምጻዊ ቴድሮስ ታለ ዩቲዩብ እና ዓለም አቀፍ በሆነው በዞጃክ ካምፓኒ በኩል በበርካታ የዲጂታል ፕላትፎርሞች ላይ ይለቀቃል። ይህን ምክንያት በማድረግም በዛሬው እለት ከቀኑ 10:00 ሰዓት ጀምሮ በደሸሾ የባህል ምግብ ቤት የአልበም ማሰማት ዝግጅት ተሰናድቷል፡፡ ይህ መርሃ ግብር የሚካሄድበት ቦታ የሚገኘው አትላስ ፊት ለፊት 2 ሺህ ሀበሻ ገባ ብሎ ነው፡፡
የቴአትር መርሃ-ግብር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቅዳሜ ሁለት ቴአትሮች ለእይታ ይበቃሉ። ቀን 8፡30 ሰዓት ላይ “12ቱ እንግዶች” እንዲሁም 11፡30 ሰዓት “ባሎችና ሚስቶች” ለእይታ ይበቃሉ፡፡ እሁድ በ8፡30 ሰዓት “ንጉሥ አርማህ” እንዲሁም 11፡30 ሰዓት ላይ “እምዩ ብረቷ” ይታያሉ። በሀገር ፍቅር ደግሞ “የመጨረሻው ፍርድ” እሁድ በ11:30 ሰዓት ይታያል፡፡
በጊዜው አማረ