ለባለተሰጥኦዎች መስታወት  የሆነው ውድድር አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የኪነ ጥበብ ዘርፉን በማሳደግ ረገድ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል

You are currently viewing ለባለተሰጥኦዎች መስታወት  የሆነው ውድድር አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የኪነ ጥበብ ዘርፉን በማሳደግ ረገድ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል

ባለፈው ረዕቡ የገና በዓል ዕለት በአዲስ ታለንት ሾው መድረክ ላይ የታየው ድምቀትና የተሰሙት አዳዲስ የጥበብ ድምፆች ለኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪ አዲስ ተስፋን ያሳየ ነው። አዳዲስ ወጣቶች በራሳቸው ቀለምና ተሰጥኦ በመድረኩ ደምቀው ታይተዋል። ሁሉም ዘመን የራሱ ኮከቦች አሉት እንደሚባለው፣ በአዲስ ታለንት ሾው የታዩት ባለ ተሰጥኦዎች ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪም ሆነ ለሌሎች የጥበብ ዘርፎች አዲስ ተስፋን የሚያሳዩ ዕንቁዎች ናቸው፡፡ ውድድሩ ሲጠናቀቅ አሸናፊዎች የአሸናፊነት ዘውድ መድፋት ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገሪቱ የኪነ ጥበብ ዘርፍ አዳዲስ ኮከቦች እየመጡ መሆናቸውን አሳይቷል። እንደ አዲስ ታለንት ሾው ያሉ የተሰጥኦ ማሳያ መድረኮች ከመዝናኛነት ባለፈ፣ የወጣቶችን ተሰጥኦ በማውጣት፣ ለኢንዱስትሪው አዳዲስ ኮከቦችን በማስተዋወቅና ለኪነ ጥበባዊም ዕድገት የሚጫወቱት ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ይሄን መነሻ በማድረግ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ተዘጋጅቶ እንደቀረበው የአዲስ ታለንት ሾው አይነት ውድድሮች ለኪነ ጥበብ እድገትና ወጣቶች ተሰጥኦዎቸውን እንዲያሳዩ በማድረግ ረገድ ምን አይነት ፋይዳ አለው? የሚለውን በጨረፍታ ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡

የአዲስ ታለንት ሾው የአንድ ዓመት ጉዞ

ለአንድ ዓመት የዘለቀው የአዲስ ታለንት ሾው የገና በዓል ዕለት (ባለፈው ረዕቡ) በዓድዋ ድል መታሰቢያ ፍጻሜዉን አግኝቷል፡፡ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በልዩነት የመጣው አዲስ ታለንት ሾው በሰባት ምዕራፎች ነበር ሲካሄድ የቆየው። ከፍተኛ ሽልማት በተዘጋጀበት በዚህ ውድድር ላይ በሦስት ዘርፎች ማለትም በሙዚቃ፣ በሰርከስ እና በትወና ዘርፎች የአሸናፊዎች አሸናፊ ተወዳዳሪዎች በመድረክ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በዚህ የፍጻሜ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪ ላይ የራሳቸውን አሻራ ማኖር የሚችሉ አስደናቂ ብቃትና ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች ታይተዋል፡፡

ትልቅ ፉክክር የታየበት የአዲስ ታለንት ሾው ውድድር በድንቅ አዘፋፈንና ችሎታ በዳኞችና በተመልካቾች የተደነቀችው ሀያት ረመዳን አሸንፋለች፡፡ ሀያት ረመዳን የአዲስ ታለንት ሾው አሸናፊ በመሆንዋ የ2 ሚሊየን ብር ተሸላሚ ሆናለች፡፡ በተጨማሪም የስኬት ባንክ ያዘጋጀውን ስኬት አዋርድ ዋንጫን ማግኘት ችላለች።

በአዲስ ታለንት ሾው የማጠናቀቂያ ውድድር ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ባህል እና ኪነ ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ አዲስ ታለንት ሾው አዲስ አበባ የጥበብ ከተማ እንድትሆን የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቢሮአቸው ኪነ ጥበብ እንዲያድግ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የጠቀሱት ኃላፊዋ በከተማዋ 320 ጀማሪ የኪነ ጥበብ ቡድኖች ይገኛሉ። እነዚህ ቡድኖች በኢንዱስትሪው ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው እንዲወጡ እንደ አዲስ ታለንት ሾው አይነት ውድድሮች አጋዥ ናቸው ብለዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ኪነ ጥበብ እንዲያድግ በርካታ ተግባራትን እየፈፀመ ነው፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ለዚህ አጋዥ ሆኖ በመምጣቱ ሊመሰገን እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ  አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው፣ ሚዲያው በኪነ ጥበብ ዘርፉ ሙያና ሙያተኛውን በማገናኘትና ዘርፉን በማሳደግ የትውልድ ድምፅ ሆኖ  በማገልገል ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አቶ ካሳሁን በንግግራቸው፣ የትውልድ ድምፅ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር ከተማዊ፣ ሀገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ይዘቶችን በፍጥነትና በጥራት ተደራሽ በማድረግ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። አዲስ አበባ ከዕለት ወደ ዕለት አስደማሚ ለውጦችን እያስመዘገበች መምጣቷን ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ ከተማዋ ያላትን  የቱሪዝም መዳረሻ ከማስተዋወቅና የኪነ ጥበብ ዘርፉን በማሳደግ ረገድ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በተገኙበት የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ የተከናወነውና  ፍፃሜውን ያገኘው አዲስ ታለንት ሾው በዘርፉ ከተሰሩት ስራዎች ቀዳሚ ማሳያ ነው። ውድድሩ መዘጋጀቱ ከማዝናናት ባለፈ የመዲናዋ ወጣቶች በሚፈልጉት የጥበብ ዘርፍ ራሳቸውን ፈልገው እንዲያገኙ ትልቅ እድል ፈጥሯል፡፡ ኤ ኤም ኤን በዘርፉ ሙያና ሙያተኛውን በማገናኘት የትውልድ ድምፅ ለመሆን ያስቀመጠውን ርዕይ በተግባር ያረጋገጠበት ነው ብለዋል።

የአዲስ ታለንት ሾው ትሩፋቶች

ናሆም ፍቃዱ የሰላሳ ዓመት ወጣት ነው፡፡ አዲስ አበባ መሳለሚያ አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ የሙዚቃና የዳንስ ከፍተኛ ፍቅር አለው። እስካሁን ድረስ በተለይ የዳንስ ፍቅሩ እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ በትምህርት ቤት የተለያዩ መድረኮች ላይ በመደነስ በተማሪዎች ዘንድ በስፋት ይታወቅ ነበር። የዳንስ ፍቅሩን በዕውቀት ላይ ለማስደገፍ አጫጭር ስልጠናዎችን ወስዷል፡፡ ነገር ግን ናሆም በልጅነቱ ፕሮፌሽናል ዳንሰኛ ለመሆን ያለመውን ህልሙን ከዳር ማድረስ አልቻለም፡፡ የዚህን ምክንያት ለአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ሲገልጽ፣ የግል ተሰጥኦና ችሎታ ማሳያ መድረኮች ከዓመታት በፊት ባለመኖራቸው፣ በዙርያዬ ያሉ ሰዎች እንደ ዳንስ ላሉ ጥበቦች ዋጋ ካለመስጠትና ተሰጥኦውን እንዲያሳድግ አይዞህ ባይ ባለማግኘቱ እንደሆነ አጫውቶናል፡፡ ናሆም አሁን ላይ በሌላ የሥራ መስክ ተሰማርቶ ውጤታማ ህይወት እየኖረ ቢሆንም፣ በተለይ ወጣቶች የሚወዱትና ውስጣቸው ያለውን ተሰጥኦ እንዲያወጡ የሚያደርጉ ምቹ መድረኮችን መፍጠር ከተቻለ ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አጫውቶናል፡፡

በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እየተዘጋጀ የሚቀርበውን የአዲስ ታለንት ሾው እንደተከታተለ ያጫወተን ናሆም፣ በተለይ አዲስ አበባ ለሚገኙ ወጣቶች ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው ተናግሯል። እንደ ናሆም ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚዘጋጁ ሌሎች ታለንት ሾዎች በተለየ፣ አዲስ ታለንት ሾው ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ከዚህ ቀደም ውስን በሆኑ ተሰጥኦዎች ላይ ይደረጉ የነበሩ ውድድሮች ወሰናቸውን በማስፋት የተለየ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች መድረክ እንዲያገኙ ማድረጉ ለወጣቶችና ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አጫውቶናል፡፡

ብዙውን ጊዜ ድብቅ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች በቂ የገንዘብ አቅም ወይም የትውውቅ መስመር (Networking) ስለሌላቸው ብቻ ችሎታቸውን ሳይጠቀሙበት ይቀራሉ። እንደ አዲስ ታለንት ሾው ያሉ ውድድሮች ግን ይህንን “የማህበራዊ ካፒታል” ክፍተት ይሞላሉ። ከዚህ አንጻር አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ መሰል የተሰጥኦ ውድድሮች ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በመረዳት ውድድሮች ማድረግ መቀጠል እንዳለበት አጫውቶናል፡፡

የውድድሩ አሸናፊዋ ሃያት ረመዳን የፍጻሜው ውድድሩን በማሸነፏ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማት ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የተናገረች ሲሆን፣ “ውድድሩን አሸንፋለሁ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር። ትልቅ የህይወትና የጥበብ ጉዞ አድርጌያለሁ፡፡ ይሄን ሁሉ ጉዞ አልፌ ማሸነፍ በመቻሌ እጅግ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ የወጣቶች ተሰጥኦ ጎልቶ እንዲታይና እንዲሸለሙ ምቹ ሁኔታዎችን ያመቻቸውን አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን አመስግናለች፡፡ በአዲስ ታለንት ሾው አማካይነት ራሴን በሚገባ እንዳሳይና ተሰጥኦዬን እንዳወጣ አድርጎኛል። እንደ ሙዚቀኛ ስሜን እንዲጠራ ያደረኩት በዚህ ታለንት ሾው አማካይነት ነው። በዚህ የታለንት ሾው ውድድር በመሳተፌም ትልቅ ክብር ተሰምቶኛል” ስትል ስሜቷን አጋርታለች፡፡

የሙዚቃ ባለሙያና ሃያሲ ሰርጸ ፍሬስብሃት ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሰጠው ሙያዊ አስተያየት፣ የታለንት ሾው የተሰጥኦ ውድድሮች በጣም እያደጉና እያበቡ ለመምጣታቸው በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ተዘጋጅቶ የቀረበው አዲስ ታለንት ሾው አንዱ ማሳያ ነው። ሁሉም የጥበብ ዘርፎች የቀረቡበት መንገድና ችሎታ በጣም እንዳስደነቀው ተናግሯል፡፡ 

የአዲስ ታለንት ሾው ዳኛ የሆነው ተክሉ አሻግሬ በተለይ ስለ አሸናፊዋ ሃያት የተሰጣትን ሙዚቃ የራሷን ፈጠራ በመጨመርና በማሳደግ ረገድ የተዋጣላት ተወዳዳሪ እንደሆነች ተናግሯል፡፡ ፈጠራዎችን አክሎ መምጣት ትልቅ በራስ መተማመን እንደሚጠይቅ በመጠቆም፣ የአዲስ ታለንት ሾው አሸናፊዋን አድንቋል። ሃያት ረመዳን ነገ ከነገ ወዲያ በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ሙዚቃን በብቃት መጫወት እንደምትችል የተናገረው ዳኛ ተክሉ፣ አዲስ ታለንት ሾው ለኢንዱስትሪው ከሚያበረክታቸው ትልልቅ አስተዋጽኦዎች መካከል አንዱ እንደ ሀያት ያሉ ባለተሰጥኦ ወጣት ሙያተኞች ናቸው ብሏል፡፡

ሃያትን ጨምሮ መድረክ ላይ ተሰጥኦቸውን ያሳዩ ተወዳዳሪዎች ትልቅ አቅም እንዳላቸው የጠቀሰው ዳኛ ተክሉ፣ “ልክ እንደ ስያሜው ሁሉ ተወዳዳሪዎች አዲስ ታለንት ነው በመድረኩ ላይ ያሳዩት። ይሄ ነው አዲስ ታለንት ማለት፡፡ አዲስ ታለንት ሾው ብዙ አይነት ታለንት ያላቸው ወጣቶች ወደ መድረክ ማምጣቱን ዳኛ ተክሉ አድንቋል፡፡ ብዙ ጊዜ በሀገራችን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የበፊቱን እያደነቅንና እሱን እየወረስን እንድንሄድ የሚያደርግ አዝማሚያ አለ፡፡ አዲስ ታለንት ሾው ግን ይሄን አካሄድ ሰብሮታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በታለንት ሾው ላይ ለፍጻሜ የደረሱ ተወዳዳሪዎችን ሳስብ አዳዲስ ኮከቦችን የማውጣትና ለኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪውም ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሆነ አስባለሁ” ሲል በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የተዘጋጀው አዲስ ታለንት ሾው ያደረገውን አስተዋጽኦ አድንቋል፡፡  

እንደ አዲስ ታለንት ሾው ያሉ ውድድሮች ከአዝናኝነታቸው ባለፈ ለአንድ ሀገር የጥበብ ዕድገት   ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው። እነዚህ መድረኮች በዘርፉ ላይ ኢንቨስትመንት ፈሰስ እንዲደረግ፣ አዳዲስ የጥበብ ቴክኖሎጂ ግብዓቶች በማስተዋወቅ እና የኪነ ጥበብ ስራዎች የገበያ ዋጋ እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ አላቸው። በተለይም በታዳጊ ሀገራት ውስጥ መደበኛ የጥበብ ትምህርት ቤቶች የማይደርሱባቸውን የተደበቁ ተሰጥኦዎች በማውጣት፣ በጥበብ ኢንዱስትሪው በየጊዜው አዳዲስ ኮከብ እንዲመጣ ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡

የታለንት ሾው ውድድር ካነሳን አይቀር የአሜሪካው “ጎት ታለንት”ን (America’s Got Talent) አለማስታወስ አይቻልም። እ.ኤ.አ. በ2006 የተጀመረው ይህ ውድድር፣ ዛሬ ላይ ከ70 በላይ ሀገራት የራሳቸውን “Got Talent” እንዲያዘጋጁ መንገድ ከፍቷል።

የአሜሪካው የጎት ታለንት ሾው ውድድር በዓለም ላይ ካሉ የታለንት ሾዎች ሁሉ በስፋቱ፣ በጥራቱና ስኬታማ የሆኑ ኮከቦችን በማውጣት ረገድ እንደ ቀዳሚ ማመሳከሪያ (Bench mark) ይወሰዳል። ይሄ ታለንት ሾው ከሚታወቅባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የተሰጥኦ ስብጥርና አካታችነት ነው፡፡ የብዙ የታለንት ሾዎች ድክመት በአንድ ዘርፍ (ለምሳሌ በድምፅ ብቻ) ላይ ማተኮራቸው ነው። የአሜሪካው ጎት ታለንት ግን “ጥበብ ወሰን የላትም” የሚል መርህን ይከተላል። ሙዚቀኞች፣ ዳንሰኞች፣ ኮሜዲያኖች፣ የሰርከስ ተወዳዳሪዎች እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አቅራቢዎች… በአንድ መድረክ ይወዳደራሉ። ይህ ደግሞ የተመልካቹን ቁጥር ከመጨመሩም በላይ፣ በሀገር ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ የፈጠራ ዘርፎች እውቅና እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አዲስ ታለንት ሾውም የዚህ አይነት ዓለም አቀፍ ልምዶችን መጠቀሙ አዳዲስ ባለተሰጥኦዎች እንዲወጡ የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡

የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪው ያለ አዳዲስ ባለተሰጥኦዎች ሊያድግ አይችልም። እንደ አዲስ ታለንት ሾው ያሉ ውድድሮች ለኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪው ትልቅ ግብዓት ይሆናሉ፡፡ ውድድሮቹ ከፍተኛ ፉክክር ያለባቸው በመሆኑ፣ ተወዳዳሪዎች የተሻለ ብቃት ይዘው እንዲመጡ ያስገድዳቸዋል። ይህ ደግሞ በጠቅላላው የኪነ ጥበብ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን የጥራት ደረጃ (Standard) ከፍ ያደርገዋል፡፡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አዳዲስ ባለተሰጥኦዎች የሚገኙባቸው አውደ-ርዕዮች ናቸው። በውድድሩ ላይ የታዩት ወጣቶች ከዛሬ ጀምሮ በበርካታ ስቱዲዮዎች ዓይን ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ ነው። ከሙዚቀኞቹ ባሻገር ለዲዛይነሮች፣ ለድምፅ መሃንዲሶች፣ በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ ማድረግ ለሚፈልጉ ባለሙያዎችና ለቴክኒሻኖች ሰፊ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ።

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review