- በጉለሌ ክፍለ ከተማ 1 ሺህ 500 ሰው የሚይዝ ሞል ለሽመና ባለሙያዎች መገንባቱ ተጠቁሟል
- በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት 800 ሱቆች በሽሮ ሜዳና አካባቢ ተገንብተዋል ፤ ለ2 ሺህ ወጣቶችም የስራ ዕድል ተፈጥሯል
- ክፍለ ከተማው ለከተማ ግብርና አመቺ ፀጋ ያለው በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል
በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ስር በሚገኘው የእንጦጦ ተራራ ላይ በአካል ቆሜያለሁ፡፡ በመንፈሴ ግን ከእንጦጦ ማርያም እስከ ሼህ ሆጀሌ አልሀሰን የዕምነትና የታሪክ መናገሻዎች፣ ከጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል እስከ ሽሮ ሜዳ፣ ከ6 ኪሎ እስከ የቆምኩበት እንጦጦ ተራራ ድረስ ያሉ የክፍለ ከተማውን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብቶችን እየዳሰስኩ ነው፡፡
በእርግጥም ጉለሌ የብዙ ታሪካዊ ስፍራዎች መገኛ፣ የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆኑ የሸክላና ሽመና ውጤቶች ማምረቻና መሸጫም ስፍራ ነው። በእርጥብ እንጨት ደም አፋሳሽ ጠብን የሚያደርቁት፣ በሽመና ስራም የተካኑት የጋሞ ማህበረሰብ በዛ ብለው ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በፍቅር የሚኖሩበት ሽሮ ሜዳም በዚሁ ክፍለ ከተማ ይገኛል፡፡
መቼም እንጦጦ ተራራ ላይ ዕድል ገጥሞት የወጣ ለስጋውም ለመንፈሱም የሚሆን አያጣም፡፡ ትንሽ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ያለውን ሁኔታ ላየና ላስታወሰ ደግሞ በእንጦጦ ተራራ ዙሪያ እንጨት ተሸክመው የሕይወትን ዳገት ይወጡ፣ ይወርዱ የነበሩ እናቶችን ማስታወሱ አይቀርም፡፡
አዎ! ሴትነት ትልቅ የተፈጥሮ ፀጋ ነው፡፡ በሴትነት ውስጥ እናትነት አለ። እናትነት ደግሞ “ሰው ሆኖ ሰው መፍጠር” ያለበት ግሩም በረከት ነው። እናት ልጆቿን ለማሳደግ የማትገፋው ተራራ፤ የማትፈነቅለው ቋጥኝ እንደሌለ ከብዙዎቻችን የልብ ማህደር የማይጠፋው የብዙነሽ በቀለ “የእናት ውለታዋ” የተሰኘው ስራዋ ሚዛን ይደፋል፡፡
የእናት ውለታዋን ባወሳ እወዳለሁ፣
ደግነቷ ብዙ መሆኑን አውቃለሁ፡፡
ዘወትር ይሰማኛል የእማዬ ድካሟ፣
ጥራ በማሳደግ በሴትነት አቅሟ…። ትላለች፤ ብዙነሽ፡፡ በእርግጥም ሴቷ በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ የችግር ተራራዎችን ትወጣለች፤ ትወርዳለች። ይህንን እውነት በእጅም በመንፈስም ለመዳሰስ እስኪ ወደ እንጦጦ ተራራ አብረን ከፍ እንበል፡፡
በእንጦጦ ፓርክ መግቢያ በስተቀኝ አቅጣጫ የተራራው ጫፍ አካባቢ እንጨት ይለቅሙ የነበሩ እናቶችን ለማስታወስ በብረት የተሰራውን ሀውልት በእጃችን እየዳሰስን በመንፈስ ደግሞ በእንጦጦ ተራራ አካባቢ እንኳን ለሰው ለማሽን የሚከብድ እንጨት በጀርባቸው አዝለው አቀርቅረው ይጓዙ የነበሩ እናቶችን እያስታወስን የዚሁ ታሪክ ባለቤትና የአካባቢው ነዋሪ ከሆኑት ወይዘሮ አዳነች ተፈራ ምስክርነትን እናገኛለን፡፡
ወይዘሮዋ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከቀን ስራ ጀምሮ ያልሰሩት የጉልበት ስራ የለም፡፡ በርካታ የዕድሜያቸውን ማምሻ ያሳለፉት ግን ቅጠል ለቅመው፣ እንጨት ሰብስበው በጀርባቸው እየተሸከሙ በመሸጥ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተማሪዎች ምግብ፣ የደንብ ልብስ እና የመማሪያ ቁሳቁስ ከማቅረቡ በፊት “እኔ ሳልማር ልጆቼም እንደኔ መሃይም መሆን የለባቸውም በሚል፣ እንጨት ለቅሜ በማገኘው ገቢ ደብተር፣ እስክርቢቶና ለመማር የሚያስፈልጉ ሌሎች ግብዓቶችን ሁሉ አሟልቼ ነበር፤ ልጆቼን የማስተምራቸው፡፡” የሚሉት እኝህ እናት ለዚህም ሲሉ ሲታመሙ፣ ነፍሰ ጡር ሲሆኑና ወልደው እንኳ በቂ እረፍት እንደማያደርጉ ከትዝታ ማህደራቸው እየጨለፉ አጫውተውናል፡፡
አስተያየት ሰጪዋ የልጆቻቸውንና የቤተሰባቸውን ልብስም ሆነ ቀለብ ለማሟላት የሚያስችል ሌላ ገቢ ስለሌላቸው ወልደው እንደሴት በቅጡ አለመታረሳቸውና በተደጋጋሚ የስራ ጫና ማሳለፋቸው ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ለጉዳት እንደዳረጋቸውም ያስታውሳሉ፡፡
ወይዘሮዋ ቀኑን ሙሉ ጭራሮ እንጨት ለቅመውና በየመንደሩ አዙረው 60 እና 70 ብር በመሸጥ መራር ሕይወትን ከመግፋታቸውም በላይ እንጨቱ እየጠፋ፣ ዕድሜ እየገፋ እና ጉልበት እያጠረ ሲሄድ ተስፋ መቁረጥ እየመጣ መሄዱንም አልሸሸጉም። የጉለሌ የተቀናጀ ልማት ግን ይህንን አስከፊ ሕይወት እንደቀየረላቸው በፈገግታ ገልፀውልናል፡፡
በእርግጥም በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ አካባቢ የተገነባው የጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራ በዋነኛነት በአካባቢው እንጨት ከጫካ በመልቀም ለሚተዳደሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል የፈጠረ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ባሳለፍነው ዓመት (ሚያዝያ ወር 2017 ዓ.ም) ላይ ወደ አገልግሎት መግባቱ ይታወሳል፡፡
ማዕከሉ 450 ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ የተገጠመለት፣ ዘመናዊ የሊጥ ማቡኪያ ማሽን፣ ዘመናዊ የአብሲት መጣያ ማሽን እና ሁለት ወፍጮዎች ያሉት ሲሆን፣ ከ550 በላይ እናቶች ወደ ስራ ገብተው በተሻለ የሕይወት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ ወገሴ ይናገራሉ፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ በተፈጥሮ ሀብትና በሰው ሰራሽ በረከቶች የታደለ መሆኑን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ፣ ከምንም በላይ ትልቁ ሀብታችን ህዝባችን ነው! ለዚህ ደግሞ የክፍለ ከተማው ነዋሪ በስነ ምግባሩ፣ በህብረ ብሔራዊነቱ እና በስራ ወዳድነቱ የሚታወቅ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
ክፍለ ከተማው፣ በሽመናና ሸክላ ስራ የተሰማሩ ወርቃማ የጥበብ እጆች ያሉበት ቢሆንም ከለውጡ በፊት የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ በእንጦጦ ተራራና አካባቢው እንጨት በመልቀም ይተዳደሩ የነበሩ እናቶችን ጨምሮ በርካታ ማህበረሰብ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሕይወቱን ለመምራት ተገድዶ እንደነበር አውስተዋል፡፡
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ በተለይም ጉለሌ በክፍለ ከተማ እንደ ወረዳ 6ን የመሳሰሉ የተጎሳቆሉ አካባቢዎች እንደ ንስር ታድሰው፣ ድፍርስና የተበከሉ ወንዞች እንደ ምንጭ ውሃ ኩልል ብለው፣ ሽሮ ሜዳን የመሳሰሉ የክፍለ ከተማው መለያዎች ታሪክና ለዛቸውን ጠብቀውና በዘመናዊ መልክ ታድሰው ደግሞም በእንዝርት መልክ የተሰራ ማራኪ መናፈሻንም ጨምሮ ልክ እንደ ሙሽራ በውበት ላይ ውበትን ደርቦ የነዋሪውን ብቻ ሳይሆን የአላፊ አግዳሚውን ቀልብ እየሳበ ነው። ይህንንም ተከትሎ ክፍለ ከተማውን የንግድና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡
አዲስ ልሳን ጋዜጣም እየታዩ ካሉ ስኬቶች ባሻገር ለመሆኑ በሸክላና በሽመና ዘርፎች የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የግብዓት፣ የመስሪያና የመሸጫ ስፍራዎች እና መሰል ችግሮች በተደጋጋሚ ያነሳሉ፤ ለዚህ ምን ምላሽ አላችሁ ስትል ጠይቃለች፡፡
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ፣ በእነዚህ ሙያዎች የተሰማሩ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ትልቅ ፀጋዎች ናቸው፡፡ ይህንንም መሰረት በማድረግ ቀደም ሲል በየቤታቸው በአስቸጋሪ ሁኔታና አካባቢ ሆነው የሸክላ ውጤቶችን ሲያመርቱ ለነበሩ እናቶች ‘እንስራ’ ዘመናዊ የሸክላ ውጤቶችን ማምረቻና መሸጫ ማዕከል ተገንብቶላቸዋል፡፡
ከመንግስት ድጋፍ ባሻገርም በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በራሳቸው አቅም ምርቶቻቸውን እስከ ውጪ ሀገር የሚልኩበትን ዕድል ፈጥረዋል። የቱሪስቶችም መዳረሻ ሆነዋል፡፡ ሲያጋጥማቸው የነበረውን የአፈር ችግር ራቅ ካለ ቦታ ለማቅረብና የተሻለ የገበያ ትስስር ለመፍጠርም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሽመና ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሚያነሱትን የግብዓት አቅርቦት ለመፍታትም የጅምላ አቅራቢ ነጋዴዎች ጋር በመነጋገር ምርቱን በቀላሉ የሚያገኙበትን ዕድል ለመፍጠር ውይይት እየተደረገ ነው፡፡ ለፋይናንስ እጥረትም የብድር አቅርቦት ለማመቻቸት ከስኬት ባንክ ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ዕድል በሚገባ እንዲጠቀሙበትም የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ለሽመና ባለሙያዎች ትልልቅ የገበያ ሞሎች መሰራታቸውን እና በኮሪደር ልማቱም እስከ 1500 ሰው የሚይዝ ሞል መገንባቱንም ተናግረዋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ያመጣውን በረከት ተከትሎ 800 ሱቆች በሽሮ ሜዳና አካባቢ መገንባታቸውን እና ለ2 ሺህ ወጣቶችም የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰው፣ ይህም ያለንን ፀጋ በሚገባ ለመጠቀም የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም በአካባቢው የተገነቡ ዘመናዊ የመስሪያና የመሸጫ ስፍራዎች ቀደም ሲል ከነበረው የተሻለ መሆኑንም ከተጠቃሚዎቹ አንደበት ሰምቷል፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚው እንደሚሉት በክፍለ ከተማው ባሳለፍነው ዓመት ብቻ ለ37 ሺህ ወጣቶች ስራ ዕድል ተፈጥሯል። በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት ደግሞ ከ10 ሺህ በላይ የስራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፣ እስከ ሁለተኛው ሩብ ዓመት ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዷል፡፡ ከስራ ፈጣሪ የግል ተቋማት ጋር በመሆንም ሰፋፊ ዕድሎችን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በአንድ ጀንበር የስራ ዕድል መርሃ ግብርም 2 ሺህ ዜጎችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉንም አቶ ወልዴ ጠቅሰዋል፡፡
በሰው ተኮር መርሃ ግብርም በክፍለ ከተማው ባሉ ሁለት የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት በቀን ከ 1 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የምገባ አገልግሎት እያገኙ ነው። ከዚህ ባሻገርም ባለፈው ክረምት ብቻ 195 ለመኖሪያ ምቹ ያልሆኑ የድሃ ቤቶች በዘመናዊ መልኩ ተገንብተዋል፡፡
ክፍለ ከተማው ለከተማ ግብርናም አመቺ ፀጋ ያለው በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው ለአብነትም ሰዎች በግቢያቸው አምርተው እንዲጠቀሙ የማድረግ፣ ለአቅመ ደካሞች ከለጋሾች ጋር በመሆን ጫጩት በማቅረብ ከዶሮ እርባታ እና ከእንቁላል ምርት ተጠቃሚ እንዲሆኑና የተረፋቸውንም በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው፡፡
ክፍለ ከተማው ለከተማ ግብርና ሰፊ ትኩረት በመስጠት በከብት እና በዶሮ እርባታ እንዲሁም መሰል የከተማ ግብርና መስኮች እየተሰሩ ካሉት ተግባራት በተጨማሪ የንብ ክላስተር ያለው ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥም የዶሮ ክላስተር እና የአሳ ፖንዶችን በስፋት ገንብቶ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ማቀዱንም የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ ተናግረዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ