ልጆች፤ እንዴት ናችሁ? ደህና እንደምትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። መታዘዝ የሚለው ቃል ለጆሮአችሁ አዲስ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ብዙ መገለጫዎች እና ጥቅሞች አሉት፡፡ ስለዚህ እናንተ ልጆች ይህን በሚገባ በመረዳት ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባችኋል፡፡ በዚህ ዙሪያ የተለያዩ ልጆችን አነጋግረን ለእናንተ ትምህርት ይሰጣል ብለን ያሰብናቸውን እንደሚከተለው እንድንነግራችሁ ወደድን፡፡
ፀጋ መንገሻ እባላለሁ ቤተሰቦቼ ማንኛውንም ትዕዛዝ ሲያዙኝ እታዘዛለሁ። ሱቅ እላካለሁ፣ እቃ አጥባለሁ፣ ቤት አፀዳለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወላጆቼ አታድርጊ የሚሉኝን ነገር ባለማድረግም እታዘዛለሁ። ለታላላቆቼ ብቻም ሳይሆን ቤት ውስጥ ላሉ ትናንሽ እህትና ወንድሞቼ የሚያስፈልጋቸውን ነገር አደርጋለሁ። የእውቀት እናትና አባቴ ለሆኑ መምህሮቼም ወደ ክፍል ሲገቡ ከክፍል ጓደኞቼ ጋር ተነስተን በመቀበል፣ የክፍል እና የቤት ስራዎች ሲሰጡ ሰርቶ በመምጣት ትዕዛዛቸውን እፈፅማለሁ፡፡
ታዛዥ መሆኔ ብዙ ጥቅም አስገኝቶልኛል፤ ከነዚህም ውስጥ የመጀመሪያው ደስተኛ እሆናለሁ። በመቀጠልም ያዘዙኝ አካላት ይደሰታሉ። መጥፎ ስነ ምግባር እንዳይኖረኝ አድርጎኛል፡፡ አንብቢ ስባል በማጥናቴ በትምህርቴ ላይ ጎበዝ እንድሆን ረድቶኛል፡፡ ለውጤቴም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቶልኛል። በቤተሰቦቼና መምህሮቼ ተወዳጅነትን አትርፌበታለሁ።
ይድነቃቸው መለሰ እባላለሁ እናቴ የምችለውን ስራ ስታዘኝ ቃሏን አከብራለሁ፡፡ የስራ እና የጥናት እንዲሁም የጨዋታ ተብሎ ተከፋፍሎ በወጣልኝ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተግባሮቼን አከናውናለሁ፡፡ ምንም ነገር ታዝዤ “አላደርግም” ብዬ አላውቅም፡፡
የትምህርት ቤት መምህራንን አከብራለሁ፡፡ የቤት ስራም ይሁን የክፍል ስራ ሲሰጡኝ በአግባቡ እሰራለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአግባቡ አጠናለሁ። በዚህም የ6ኛ ክፍል የሚኒስትሪ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ችያለሁ፡፡ ታዛዥ በመሆኔ እናቴ በእኔ ትመሰገናለች። ቤተሰቦቼም ሆነ እኔ በዚህ ደስታ ይሰማናል፡፡
ቤዛ መሰለ እባላለሁ በቤተሰቦቼም ይሁን በትምህርት ቤት መምህራን የምታዘዘውን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ ስለማይፈቅዱልኝ ስልክ አልጠቀምም። ትምህርት ቤትም ከደብተርና እስኪርቢቶ ውጭ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ይዘን እንዳንገባ እንከለከላለን፡፡ ይህንንም ተግባራዊ አደርጋለሁ፡፡ እሺ ብዬ ማድረጌ ከእድሜዬ ጋር የማይሄዱ ነገሮችን እንዳላደርግ እንዲሁም ችግሮች እንዳይገጥሙኝ አግዞኛል፡፡ ትኩረቴንም ትምህርቴ ላይ እንዳደርግ ረድቶኛል፡፡
ዳግም ጤና እባላለሁ ቤተሰቦቼም ሆኑ መምህራኖቼ አድርግ ያሉኝን እፈፅማለሁ፡፡ ወላጆቼን በስራ አግዛለሁ። የመምህራኖቼን ምክር እሰማለሁ፤ ይህንንም መተግበሬ ጥሩ ስነ ምግባር እንዲኖረኝ ረድቶኛል፤ በታላላቆቼ እንድመረቅ አድርጎኛል፤ በሰዎች ዘንድም ተወዳጅነትን አትርፎልኛል፡፡
መታዘዝ የሚያስፈልገን ነገር እንዲደረግልን ይጠቅማል፡፡ ለዚህም እኔ ለታላላቆቼ ብቻ ሳይሆን ታናናሾቼንም እንድታዘዝ ሲነገረኝ ተግባራዊ አደርጋለሁ፡፡ በዚህም ተጠቅሜበታለሁ፡፡
ልጆች፤ መታዘዝ የተሰጠንን ኃላፊነት መፈፀም ማለት ነው፡፡ ይህን ማድረግ ጥቅሙ ብዙ እንደሆነ ልጆች ከተናገሩት መገንዘብ እንደቻላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እናንተም ትንሽ ትልቅ ሳትሉ መታዘዝ አለባችሁ፡፡ ስትታዘዙ ደግሞ ቤተሰቦቻችሁና መምህራኖቻችሁ ይወዷችኋል፤ የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች ያደርጉላችኋል፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ