የመጀመሪያው የካፍ ፕሬዝዳንት በነበሩት አብደልአዚዝ አብደላ ሳሌም ስም የተሰየመውና ሱዳን አሰናድታው ግብጽ ያሸነፈችው የመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ለአሸናፊው ሀገር ያበረከተው ሽልማት ዋንጫ ብቻ ነበር። ወቅቱ ውድድሩ ገና አዲስ ከመሆኑም በላይ እንደ ዛሬው የንግድ ስፖንሰሮች እና የቴሌቪዥን ስርጭት ገቢ ስላልነበረው ለአሸናፊው የሚከፈል የገንዘብ ሽልማት አልተዘጋጀም ነበር። ለአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዎች የሚሰጥ የገንዘብ ሽልማት በይፋ እየታወቀና በከፍተኛ መጠን እያደገ የመጣው ከ1990ዎቹ በኋላ ነበር። በተለይም እ.ኤ.አ በ2002 ማሊ ላይ በተደረገው ውድድር አሸናፊዋ ሴኔጋል የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ማግኘቷ በወቅቱ ትልቅ ዜና ነበር።
በአህጉሪቱ ትልቁ የስፖርት ውድድር የሆነው የአፍሪካ ዋንጫ (AFCON) አሁን ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ፍሰት የሚታይበት ግዙፍ የቢዝነስ መድረክ እየሆነ መጥቷል። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ከዚህ ውድድር የሚያገኘው ገቢም በየዓመቱ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ይገኛል።
በኮትዲቯር በተካሄደው የ2023ቱ ውድድር በታሪክ ከፍተኛው ገቢ የተመዘገበበት ሆኗል። ለተሳታፊ ሀገራት የሚሰጠው ሽልማት እንደዚሁ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን፣ በወቅቱ ለአሸናፊው ሀገር 7 ሚሊዮን ዶላር ተበርክቷል፤ ይህም ካለፈው ውድድር ጋር ሲነጻጸር የ40 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። በሁለተኛነት ላጠናቀቀው ብሔራዊ ቡድንም እንደዚሁ አራት ሚሊዮን ዶላር ተበርክቶለታል፡፡ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ሀገራትም 2 ሚሊዮን 500 ሺህ ዶላር እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡
አራቱ የሩብ ፍጻሜ ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድኖችም አንድ ሚሊዮን 300 ሺህ ዶላር ተመድቦላቸው ነበር፡፡ የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞቴሴፔ (ዶ/ር) የአሸናፊዎች ሽልማት ከቀድሞው የገንዘብ መጠን ጋር ሲነጻጸር 40 በመቶ ጭማሪ ማድረጉ ካፍ እግር ኳስን ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለው ነበር።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከ47ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላ ባወጣው ሪፖርት በ2023/24 የውድድር ዓመት የተጣራ 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አሳውቋል።
ተቋሙ ባለፉት አራት ዓመታት ከገጠመው የገንዘብ ቀውስ ወጥቷል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ አሁን ላይ የካፍ ገቢ ወደ 166 ነጥብ 42 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል። አክለውም፣ ካፍ ትልልቅ ስም ካላቸው አጋሮች ጋር በመስራት የገንዘብ አቅሙን በማሳደግ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞቴሴፔ (ዶ/ር) በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተጽዕኖ ፈጣሪነት ላይ እየተሰራ ነው ብለው፣ ካፍ እስከ 2024/2025 የፋይናንስ ዓመት መጨረሻ ድረስ ጠቅላላ ገቢውን ወደ 250 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ ግብ እንዳለው ገልጸዋል።
እየተካሄደ ባለው የ35ተኛው የአፍሪካ ዋንጫም ካፍ በአጠቃላይ ለውድድሩ ተሳታፊ ሀገራት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የ32 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያዘጋጀ ሲሆን፣ ዋንጫውን የሚያነሳው ቡድን ከሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ ሽልማት እንደሚያገኝ ተገልጧል። ሁለተኛ ለሚወጣው አራት ሚሊዮን ዶላር ተዘጋጅቷል።
ለግማሽ ፍፃሜ ያለፉ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ሲሸለሙ፤ ሁሉም የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ 24 ሀገራት ለተሳትፏቸው ብቻ በሚቋደሱት ሽልማት ምድባቸውን አራተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ቡድኖች የ500 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ይሆናሉ። የዋንጫው አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን እና ለተሳታፊዎች በሚበረከተው የገንዘብ መጠን በዓለማችን ከሚገኙ አህጉራዊ ውድድሮች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ በአውሮፓ ዋንጫ እና በኮፓ አሜሪካ ይበልጣል ተብሏል።

እዚህ ጋር ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ታዲያ ምን ስለተሰራ የአፍሪካ ዋንጫ የገቢ አብርክቶ እያደገ ሊመጣ ቻለ? የሚለው ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ አፍሪካ ኒውስ ሞሮኮ እያሰናዳች ያለውን 35ተኛው አፍሪካ ዋንጫን ዋቢ አድርጎ የሰራው ዘገባ ምላሽ አለው፡፡ ውድድሩ ለ52 ጨዋታዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቲኬት መሸጣቸው በውድድሩ ታሪክ ክብረ ወሰን መሆኑን ካፍ አስታውቋል። በተጨማሪም በውድድሩ ከ150 በላይ ሀገራት የሚገኙ ሲሆን ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ሰዎች በቴሌቪዥን መስኮታቸው ይመለከቱታልም ተብሎ ይጠበቃል።
እስከ ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆየውን ውድድር ለመዘገብ 3 ሺህ 800 ያህል ገደማ መገናኛ ብዙሃን ፈቃድ ማግኘታቸውንም ካፍ ጨምሮ አስታውቋል። ሞሮኮ በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ነው የተባለለትን የ“4K HDR” የቀጥታ የጨዋታ ስርጭት ሙከራ አድርጋለች፡፡ “4K HDR” በዓለም አቀፍ የብሮድካስት ኩባንያዎች ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን የምስል ጥራቱ ከፍተኛ የሆነ ነው። ቀረጻው ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚቀርጹ ካሜራዎች እና ድሮኖችን ያካተተ ነው። ዓለም አቀፍ “4K HDR” የብሮድካስት ስርጭት ስርዓቱ ከዓለም ዋንጫ ጋር ተቀራራቢነት ያለው እንደሆነ ተነግሯል።
ካፍ የተከተለው የገንዘብ አስተዳደር እና አዳዲስ ስፖንሰሮች ለዚህ ትልቅ ስኬት እንዳበቁት የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞቴሴፔ ይናገራሉ። የካፍ ገቢ በዋናነት የሚመጣው ከሁለት ትላልቅ ዘርፎች ሲሆን፣ የቴሌቪዥን ስርጭት መብት (Media Rights) ትልቁ የገቢ ምንጭ ሆኗል፡፡ በተለይ ከኮትዲቯሩ የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ከዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። በንግድ ስፖንሰርሺፕም (Commercial Sponsorship) እንደዚሁ እንደ ቶታል ኢነርጂስ ዋንኤክስቤት፣ ዚቫ እና ኦሬንጅ ያሉ ኩባንያዎች የሚከፍሉት የገንዘብ መጠን ከውድድር ወደ ውድድር እየጨመረ መጥቷል።
የውድድሩ ተመልካች ቁጥር መጨመር፣ አዳዲስ ስፖንሰሮች መሳብ እና የአስተዳደር ለውጥ ካፍ ከስፖንሰሮች የሚያገኘው ገንዘብ እንዲጨምር ያደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች ተደርገው ይጠቀሳሉ፡፡
የ2023ቱ የኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ በታሪክ ከፍተኛ ተመልካች የታየበት በመሆኑ ስፖንሰሮች ብዙ ገንዘብ እንዲያፈሱ አድርጓል። በተጨማሪም ካፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ፑማ እና ሀብሽሮን ካሉ አዳዲስ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር ውል መፈራረሙና የውድድሮቹን የንግድ ዋጋ (Commercial Value) ለማሳደግ ባደረገው ጥረት የገቢ ምንጮችን ማሳደግ ችሏል። ካፍ በቅርቡ ባወጣው የፋይናንስ ሪፖርት መሠረት፣ ጠቅላላ ገቢው በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ60 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

ይህ መሰረታዊ የገቢ ዕድገት ታዲያ ለአፍሪካ እግር ኳስ ልማት እና እድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት እሙን ነው። ካፍ ለአባል ማኅበራቱ የሚሰጠውን ዓመታዊ ድጎማ ከ200 ሺህ ዶላር ወደ 400 ሺህ ዶላር ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ የእግር ኳሱ መሰረተ ልማት እንዲሻሻል ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም የተቋሙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ለአባል ሀገራት ፈሰስ የሚደረገው ገንዘብም በዋናነት ለወጣቶች ውድድር ማሳደጊያ፣ ለሴቶች እግር ኳስ ልማት እና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፕሮግራሞች እንዲውል ተወስኗል። በአህጉር አቀፍ ውድድሮች (የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ) ለሚሳተፉ ክለቦች እንደዚሁ የገንዘብ ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። በተጨማሪም ለዳኞች እና ለአሰልጣኞች የሥልጠና ፕሮግራሞች እንዲስፋፉ አስተዋጽኦው ላቅ ያለ ስለመሆኑ የካፍ ዋና ጸሐፊ ቬሮን ሞሰንጎ ኦምባ ይገልጻሉ፡፡
በእርግጥ የአፍሪካ ዋንጫው ለካፍ ብቻም ሳይሆን ውድድሩን ለሚያዘጋጀው ሀገርም ቢሆን ይዞት የሚመጣው ትሩፋት ቀላል አይደለም ይላል የአፍሪካ ኒውስ ዘጋባ። ውድድሩን የሚያስተናግዱ ሀገራት ዘመናዊ ስታዲየሞችን፣ ሆቴሎችንና የመገናኛ አውታሮችን እንዲገነቡ ይገደዳሉ። ይህም ከውድድሩ በኋላ ለሀገሪቱ ስፖርት ትልቅ ቅርስ ሆኖ ይቆያል። የአፍሪካ ዋንጫው በሞሮኮ የቱሪዝም ወቅት ውስጥ ከፍተኛ ጎብኚ በሚመጣበት ጊዜ መካሄዱ ለቱሪዝም እድገት እና ለሀገር ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ሞሮኮ በ2025 የመጀመሪያ 10 ወራት ከቱሪዝም ከ11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኘች ሲሆን፣ የአፍሪካ ዋንጫ ይህን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።
እንደ ዓለም አቀፉ ስታቲስታ የምርምር ተቋም መረጃ መሠረት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በ2023 ከተካሄደው አፍሪካ ዋንጫ የተገኘው ገቢ ከ109 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ሲሆን፣ በሞሮኮ እየተካሄደ ባለው 35ተኛው የአፍሪካ ዋንጫም ከ113 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ