የጉበት ስብ በጉበት ሴሎች ውስጥ ከመጠን ያለፈ ስብ ሲከማች የሚከሰት የጤና እክል ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ምክንያት በስፋት እየታየ ይገኛል። ስለ በሽታው መንስኤ፣ ምልክቶችና መከላከያ መንገዶች የሥነ-ምግብ ባለሙያ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን ፈቃዴ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ዝርዝር መረጃ አጋርተዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ ጉበት በተፈጥሮው ጥቂት መጠን ያለው ስብ የሚይዝ ቢሆንም፤ የተለያዩ ምክንያቶች ሲያጋጥሙ ግን ስቡ በከፍተኛ ሁኔታ ሊከማች ይችላል።
የጉበት ስብ በሁለት ዋና መንገዶች ይከሰታል ያሉት ባለሙያው፤ በአልኮል ምክንያት የሚመጣ እና ከአልኮል ጋር ግንኙነት የሌለው ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያያዘ ሊከሰት እንደሚችለ አብራርተዋል፡፡
መንሴዎቹ
ከመጠን ያለፈ ውፍረት በተለይ በሆድ አካባቢ የሚከማች ስብ፣ የስኳር በሽታ (Type 2 Diabetes) እና ኢንሱሊን በአግባቡ ስራውን ካልሰራ ስብ በጉበት ውስጥ ይከማቻል።
የተዛባ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል በተለይ ከፍተኛ ካርቦሃይድሬት፣ ስኳር እና ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን ማዘውተር፣ ከፍተኛ የአልኮል መጠጥ መጠጣት እንዲሁም ከፍተኛ የደም ግፊት እና የኮሌስትሮል መጠን መጨመር የጉበት ስብ ክምችን እንደሚፈጥር የሥነ ምግብ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡

ምልክቶቹ
የጉበት ስብ በአብዛኛው መጀመሪያ አካባቢ ምንም አይነት ግልጽ ምልክት አያሳይም፤ ነገር ግን በሽታው እየገፋ ሲሄድ በቀኝ በኩል ከደረት በታች (በጉበት አካባቢ) የመክበድ ወይም የመውጋት ስሜት፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ በሽታው ከጸና የቆዳና የዓይን ቢጫ መሆን እና የሆድ እብጠት ዋነኛ ምልክቶች ናቸው።
መከላከያ መንገዶቹ
የጉበት ስብን አስቀድሞ ለመከላከልና ካለበትም ለማገገም የሰውነት ክብደትን ቢያንስ ከ5 እስከ 10 በመቶ መቀነስ፣ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል በተለይ ፋይበር ያላቸውን ምግቦች (አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ) ማዘውተር፣ ስኳርና ነጭ ዱቄት የበዛባቸው ምግቦችን መቀነስ፣ በሳምንት ቢያንስ 150 ደቂቃ ድረስ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዲሁም አልኮልን ማቆም ወይም መቀነስ ጉበት ራሱን እንዲያድስ እድል የሚሰጥ መሆኑን የሥነ ምግብ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

ህክምናው
ለጉበት ስብ ተብሎ የታዘዘ የተለየ መድኃኒት ባይኖረውም ህክምናው የሚያተኩረው መንስኤዎቹን በማከም ላይ እንደሆነም ነው ባለሙያው የተናገሩት፡፡
የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ዋነኛውና ውጤታማው ህክምና ሲሆን፤ ተጓዳኝ በሽታዎችን መቆጣጠር እንደ የደም ስኳር፣ የግፊትና የኮሌስትሮል መጠንን በመድኃኒት መቆጣጠር ይገባል።
በመጨረሻም፣ የጉበት ስብ ችላ ከተባለ ወደ ጉበት ጠባሳ (Cirrhosis) እና ወደ ካንሰር ሊያመራ ስለሚችል፣ ምልክቶቹ የታዩበት ማንኛውም ሰው ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ የባለሙያ ምክር ማግኘት እንዳለበት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን ፈቃዴ አሳስበዋል።
በበረከት ጌታቸዉ