በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
ሚኒስትሯ ከጥር 1 እስከ 30/2018 የሚከበረውን “የጤናማ እናትነት ወር” አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ባለፉት ዓመታት ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የጤና ችግርና ሞትን ለመቀነስ በተደረገው ርብርብ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር መጨመሩን ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል በሆስፒታሎች ብቻ ይሰጡ የነበሩ የጽንስና ማዋለድ ቀዶ ሕክምናዎች በጤና ጣቢያዎች ጭምር መጀመራቸው ለውጥ ማምጣቱን አንስተው፤ የጤና ተቋማት ተደራሽነት መስፋፋት የቅድመ ወሊድ ክትትልን ማሳደጉንም አሳውቀዋል።
ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የደም መፍሰስን በመከላከል ረገድም የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ሚና እና ቁጥር መጨመሩን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
እስካሁን የተገኙ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው፣ በቀጣይም የተሻሉ ውጤታማ ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል። ለዚህም ፈጠራ እና ዘላቂ ፋይናንስ ወሳኝ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ የዲጂታል ጤና መረጃን ተደራሽ ማድረግ፣ የሕክምና ግብዓቶችን ማሟላትና የቀዶ ሕክምና አገልግሎትን ማስፋት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የዘንድሮው የጤናማ የእናትነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ39ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ ”ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮች ይከበራል።
በአልማዝ ሙሉጌታ