በ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዉስጥ ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ከ14 ቢሊየን 51 ሚሊየን 586 ሺህ በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው የገቢና ወጪ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ከ729 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ገልጸዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወር የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ እንደገለጹት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በተሰራው ሥራም 1 ሺህ 6 መቶ 12 ኮብላዮች ተይዘው ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
41 አስኮብላዮችም በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖችን እኩይ ዓላማ በማክሸፍ፤ በደቡብ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር እና በሱማሌ ክልሎች የተከሰቱ ግጭቶችን በመቆጣጠር ረገድ ጉልህ ድርሻ ተወጥቷል ሲሉ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ 625 ግዙፍ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ታላላቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን በመጠበቅ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡ በግምማው ተነስቷል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች የተካሄዱ ዓለም አቀፋዊ፤ አህጉራዊ እና ሀገራዊ ኹነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ ማድረግ ተችሏል ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እና ከሌሎች የፌደራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔን ጨምሮ በቀጣይ ስድስት ወራት የሚከናወኑ ዓለም አቀፋዊ፤ አህጉራዊ እና ሀገራዊ ኹነቶች እንዲሁም ሃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት በስኬት እንዲካሄዱ በቂ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ለፖሊስ ሠራዊቱ ተከታታይነት ያላቸው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች እንደሚሰጡም ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል በግምገማው ማጠቃለያ ላይ ማስታወቃቸዉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡