የስፓኒሽ ሱፐር ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ በሪያል ማድሪድ እና ባርሰሎና መሀከል ዛሬ ይከናወናል፡፡
ባርሰሎና አትሌቲክ ቢልባኦን ሪያል ማድሪድ ደግሞ የከተማ ተቀናቃኙ አትሌቲኮ ማድሪድን በማሸነፍ ነው ለፍፃሜ የደረሱት፡፡ የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሳውዲ አረቢያ መንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ውድድሩ ከ2019 ጀምሮ በሳውዲ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ዛሬም ጅዳህ በሚገኘው ንጉስ አብደላህ ስፖርት ሲቲ ስታዲየም የፍፃሜው ጨዋታ ይከናወናል፡፡ የስፓኒሽን ሱፐር ካፕን በማሸነፍ ሁለቱ ሃያላንን የሚስተካከል የለም፡፡
ባርሰሎና 15 ጊዜ ዋንጫውን ሲያነሳ ፣ ሪያል ማድሪድ 13 ጊዜ ማሸነፍ ችሏል፡፡ ዛሬ በሚያደርጉት ፍልሚያ በሁለቱም ክለቦች በኩል የተለየ የጉዳት ዜና የለም፡፡
በማድሪድ በኩል በጉዳት ምክንያት የአትሌቲኮ ጨዋታ ያለፈው ኪሊያን እምባፔ ወደ ስብስቡ ተመልሷል፡፡ ሁለቱ ክለቦች በተመሳሳይ ባለፈውም ዓመት በስፓኒሽ ሱፐር ካፕ ፍፃሜ ተገናኝተው ነበር፡፡
ጨዋታውን ባርሰሎና 5ለ2 አሸንፎ ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል፡፡ የዛሬ ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይጀምራል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ