የኤፍ ኤ ካፕ 4ኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይከናወናሉ፡፡ 11 ሰዓት ላይ አርሰናል ከሜዳው ውጪ ፖርትስማውዝን ይገጥማል፡፡
የፕሪምየር ሊግ አድማቂ ከነበሩ ክለቦች አንዱ የሆነው ፖርትስማውዝ አሁን ላይ በሻምፒየን ሺፕ እየተወዳደረ ይገኛል፡፡ በሊጉ 21ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ላለመውረድ የሚታገለው ፖርትስማውዝ ምንም እንኳን በሜዳው ፍራተን ፓርክ ቢጫወትም 14 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ አርሰናልን የመቋቋም እድል ያለው አይመስልም፡፡
ሚካኤል አርቴታ በተለይ በፕሪምየር ሊግ ብዙ የመጫወት እድል ያላገኙ ተጫዋቾችን ይጠቀማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተለይ ከግዳት ከተመለሰ በኋላ ጨዋታ ያላከናወነው ካይ ሃቨርትዝ ተሳታፊ ይሆናል ተብሏል፡፡

ኤቤሪቼ ኤዜ ፣ ጋብርኤል ጄሱስ ፣ ክሪስቲያን ኖርጋርድ ፣ ማይልስ ሊውስ ስኬሊ እና ቤን ኋይት እንዲሁም ሌሎች ወጣት ተጫዋቾች በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የመካተት እድል ያላቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡
በሌላ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ ምሽት 1፡30 ብራይተንን ያስተናግዳል፡፡ ዩናይትድን በጊዜያዊነት የተረከበው ዳረን ፍሌቸር በኦልድ ትራፎርድ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመራል፡፡
ፍሌቸር በፕሪምየር ሊጉ ቡድኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በመራበት ጨዋታ ከበርንሌይ ጋር 2ለ2 መለያየቱ ይታወሳል፡፡ በዛሬው ጨዋታ በዩናይትድ በኩል ከጉዳት የሚመለስ ተጫዋች የለም፡፡
ከአፍሪካ ዋንጫ ውጪ የሆኑት ብሪያን ምቡሞ እና አማድ ዲያሎ ለዛሬው ጨዋታ አይደርሱም፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ