በደቡብ ምስራቅ አውስትራሊያ በተከሰተ ሰደድ እሳት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ፣ 300 ቤቶችና ሕንፃዎችም መውደማቸው ተገልጿል።
እሳቱ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ በርካታ ቦታዎች የተስፋፋ ሲሆን፣ በአብዛኛው በቪክቶሪያ ግዛት ውስጥ፣ እንዲሁም በኒው ሳውዝ ዌልስ ውስጥ ከለንደን ከተማ እጥፍ የሚሆን መሬትን ማቃጠሉ ተሰምቷል።
በቪክቶሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እና ከ70 በላይ አውሮፕላኖች እሳቱን ለማጥፋት ርብርብ እያደረጉ ሲሆን፣ በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ታውጇል።
በአካባቢው የሚኖሩ በርካታ ዜጎችም መኖሪያቸውን ለቀው እንዲወጡ ምክር ተሰጥቷቸዋል።
እየተቀጣጠለ ያለው እሳት በአካባቢው ካለው ሞቃት፣ ደረቅ እና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ለሳምንታት ሊዘልቅ ይችላል በሚል ባለስልጣናት ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የቪክቶሪያ አስተዳዳሪ ጃሲንታ አለን፣ በግዛቱ በ30 ቦታዎች እሳት እየተቀጣጠለ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አሥሩ አሳሳቢ ናቸው ብለዋል።
እስከ አሁንም በመላ ቪክቶሪያ 350 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ጫካ ሙሉ በሙሉ እንደወደመ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በታምራት ቢሻው