ባለፋት ስድስት ወራት የሀገርና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ እንዲሁም ወንጀልን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ሥራዎችን መከናወናቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለፁ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወር የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እያካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንደተናገሩት፥ ፖሊስ ባለፉት ስድስት ወራት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከሌሎች የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የሀገርንና የሕዝቡን ሰላም እና ደህንነት በሁለንተናዊ መልኩ ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።
በወንጀል መከላከል፣በወንጀል ምርመራ፣ በሰው ኃይል ልማት፣ በሎጂስቲክስ አቅም ማሳደግና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውጤታማ ሥራ መሠራቱን አስረድተዋል።
የሽብር ኃይሎችን እንቅስቃሴ በመቆጣጠርና የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድም ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ነው ያነሱት።
ፖሊስ ባለፉት ስድስት ወራት ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ጠቅሰው፥ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርንና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን በተቀናጀ መልኩ ለመግታት ውጤታማ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቅሰዋል።
መንግሥታዊና ሃይማኖታዊ በዓላት እንዲሁም ታላላቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች በስኬት መከናወናቸውን አንስተዋል።
የፖሊስ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የላቀ የማድረግ ሥራ መጠናከሩን ጠቅሰው፥ በቅርብ ቀናት ውስጥ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ስማርት ፖሊስ ጣቢያ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የፖሊስ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራ የዜጎችን ሰብዓዊ መብትና ክብር በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ የፎረንሲክ ምርመራ አቅም እያደገ ነው ብለዋል።