ኢትዮጵያ እና ጃፓን በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸዉ ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለጸ

You are currently viewing ኢትዮጵያ እና ጃፓን በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸዉ ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለጸ

AMN ጥር 4/ 2018

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኩኒሚትሱ አያኖ ከተመራ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ጌዲዎን (ዶ/ር) ኢትዮጵያ እና ጃፓን ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው እና በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን የግንኙነት መድረኮችም ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው ገልጸዋል። ሚኒስትሩ ጃፓን ለኢትዮጵያና ለምታደርጋቸው የልማት ድጋፎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት በተለይ በንግድ እና ኢንቨስትመንት እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው የበለጠ መጠናከር እንዳለበት ዶ/ር ጌዲዎን ገልጸዋል።

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኩኒሚትሱ አያኖ በበኩላቸው የኢትዮጵያ እና ጃፓን ግንኙነት በንግድ እና ኢንቨስትመንት የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት አንስተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዎን በሚኒስትር ዴኤታዋ ተመርቶ ለመጣው ከ35 በላይ የጃፓን ኩባንያዎች ለተውጣጡ 48 የቢዝነስ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ያለውን አዲስ እና ምቹ የንግድ እና ኢንቨስትመንት በተመለከተ ሰፊ ገለጻ ሰጥተዋል። ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ኩኒሚትሱ አያኖ በበኩላቸው ለልዑካን ቡድናቸው ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው ነገ በሚካሄደው የኢትዮ-ጃፓን ቢዝነስ ፎረም እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። ፎረሙ የሁለቱን አገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ በማጠናከረ ረገድ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል መባሉን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review