የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ለግብር ከፋዩ ተግዳሮት የሆኑ አሠራሮችን በማሻሻሉ በቢሮውና በግብር ከፋዩ መካከል ያሉ ቅሬታዎች እየተፈቱ ነው

You are currently viewing የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ለግብር ከፋዩ ተግዳሮት የሆኑ አሠራሮችን በማሻሻሉ በቢሮውና በግብር ከፋዩ መካከል ያሉ ቅሬታዎች እየተፈቱ ነው

AMN – ጥር 04/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ለግብር ከፋዩ ተግዳሮት የሆኑ አሠራሮችን በማሻሻሉ በቢሮውና በግብር ከፋዩ መካከል ያሉ ቅሬታዎች እየተፈቱ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡

ቢሮው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከታክስ ውሳኔ ጋር ተያይዞ ከቀረቡለት ቅሬታዎች መካከል ለ89 በመቶዎቹ ምላሽ መስጠቱን ገልጿል።

በቢሮው የታክስ ውሳኔ ቅሬታ አጣሪ ዳይሬክተር አቶ ኤርማያስ ደጌ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በግማሽ ዓመቱ በአጠቃላይ 13 ሺህ 643 የታክስ ውሳኔ ቅሬታዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ለ11 ሺህ 892 ቅሬታዎች ተገቢው ምላሽ ተሰጥቷል ብለዋል።

ቢሮው ለግብር ከፋዩ ተግዳሮት የሆኑ አሠራሮችን በማሻሻል ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በተለይም ቅሬታዎችን በቅርበት የሚሰማና ተገቢ ባልሆኑ ውሳኔዎች ላይ ማስተካከያ የሚያደርግ ራሱን የቻለ የሥራ ክፍል ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱንም ተናግረዋል።

በቀሪዎቹ ስድስት ወራትም እስካሁን ምላሽ ያላገኙ ቅሬታዎችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

ይህ እርምጃ በግብር አሰባሰብ ሂደት ውስጥ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍና በቢሮውና በግብር ከፋዩ መካከል ያለውን እምነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

በጽዮን ማሞ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review