በአዲስ አበባ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የ”ዋይልድ ሳፋሪ” (Wild Safari) ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ “በአዲስ አበባ ወንዞች ትንሣኤ” ዘጋቢ ፊልም በአዲስ አበባ እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው የከተማ ውስጥ “ዋይልድ ሳፋሪ” በአዲስ አበባ እየተገነባ ይገኛል።
ከንቲባዋ በጉብኝታቸው ወቅት እንደተናገሩት ፤ አዲስ አበባ በዚህ ደረጃ የከተማ ዋይልድ ሳፋሪ መገንባት ከቻለች፣ የክልል ከተሞችም ካላቸው ተፈጥሯዊ ፀጋ በመነሳት ከዚህ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ትልቅ ዕድልና መነሳሳት ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።
ይህ ግዙፍ የዋይልድ ሳፋሪ ፕሮጀክት የሴግመንት ስድስት የወንዝ ልማት አካል ሲሆን፣ በ55 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው።
ከ200 በላይ የዱር አራዊትን ወደ ሳፋሪው ለማስገባት ታቅዶ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በፓርኩ ውስጥ ከ100 ዓመት በላይ ያስቆጠሩ ጥንታዊ ዛፎች የሚገኙ ሲሆን፣ ይህም ለአራዊቱ ምቹ መኖሪያ፣ ለጎብኝዎች ደግሞ ማራኪ የመዝናኛ ስፍራ እንዲሆን ተደርጎ እየተገነባ ነው።
የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን እርስ በእርስ በማስተሳሰር፣ በከተማዋ የሚገኙ ጸጋዎችን በማቀናጀትና ብቃታቸውን በማሳደግ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ከንቲባዋ ተናግረዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ