የመደጋገፍ ዕሴትን በተደራጀ አግባብ መምራት የሚያስችል የዘካ እና አወቃፍ ኮሚሽን ተቋቋመ

You are currently viewing የመደጋገፍ ዕሴትን በተደራጀ አግባብ መምራት የሚያስችል የዘካ እና አወቃፍ ኮሚሽን ተቋቋመ

AMN ጥር 4/2018

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የመደጋገፍ ዕሴትን በተደራጀ አግባብ መምራት የሚያስችል የዘካ እና አወቃፍ ኮሚሽን ሥራ መጀመሩን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዘካና አውቃፍ ኮሚሽን ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ ዘካ እና አውቃፍ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተቋማዊ ባልሆነ መንገድ ሲሰራበት ቆይቷል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሁለቱን ወሳኝ የእስልምና እምነት የአምልኮ ግዴታዎች ተቋማዊ ቅርጽ በማስያዝ የመተጋገዝ ኃላፊነትን በተደራጀ አግባብ ለመምራት መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።

በቀጣይም የዘካ እና አወቃፍ ኮሚሽን ኃይማኖታዊ መርሆዎችን በተከተለ መንገድ ማህበራዊ ፍትሕን የሚያሰፍን የችግሮች መፍቻ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የእስልምና ኃይማኖትን ታሪካዊ ዕሴት፣ የማህበራዊና መንፈሰዊ ትስስር የሚያጠናክር የዘካ እና አወቃፍ ኮሚሽን ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በዘካ እና አወቃፍ ዕምቅ አቅሙን በማጎልበት ማሕበራዊና መንፈሰዊ ትስስርን የበለጠ በማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

ዘካ እና አወቃፍ በከሚሽን ደረጃ ሥራ መጀመሩ ከመንፈሳዊ ፋይዳው ባለፈ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሕግ አሰራር ሥርዓትን የተከተለ ድጋፍ ለማቅረብ እንደሚረዳ አንስተዋል።

በቀጣይ ኮሚሽኑ በተደራጀ መንገድ ስራ ሲጀምር ለሀገር ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው በመጠቆም፤ ለኮሚሽኑ ውጤታማነትም የዜጎች ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ዘካ ማለት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በእስልምና ሃይማኖት መርሆዎች ሰዎች ካላቸው የሚያካፍሉበት ሥርዓት ነው።

አውቃፍ ደግሞ ለበጎ አድራጎት እንዲውል ታስቦ ከአማኞች የሚሰጥ ቋሚ ንብረት ማለት ነው።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1207/2012 በተሰጠው ስልጣን መሰረት የተቋቋመ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review