በቢሾፍቱ የሚገነባው አዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የአፍሪካን የአቪዬሽን ገጽታ እንደሚቀይር ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ገለጹ

You are currently viewing በቢሾፍቱ የሚገነባው አዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የአፍሪካን የአቪዬሽን ገጽታ እንደሚቀይር ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ገለጹ

AMN- ጥር 4/2018 ዓ.ም

በቢሾፍቱ የሚገነባው አዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን የአቪዬሽን ገጽታ እንደሚቀይር ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል፡፡

በቢሾፍቱ ለሚገነባው አዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት መካሄዱን ተከትሎ፣ አውሮፕላን ማረፊያው ትልቅ አቅም እንደሚኖረው ሮይተርስ ዘግቧል።

የፕሮጀክቱ ጠቅላላ ወጪ 12.5 ቢሊየን ዶላር እንደሆነና የኢትዮጵያ አየር መንገድ 30 በመቶ የሚሆነውን ወጪ እንደሚሸፍን፣ ቀሪው ደግሞ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች እንደሚገኝ ዘግቧል። አውሮፕላን ማረፊያው 270 አውሮፕላኖችን በአንድ ጊዜ ማቆም እንደሚችልም ጠቁሟል።

የፕሮጀክቱን አዋጭነትና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን በጥልቀት የተነተነው ደግሞ ዘ ኢኮኖሚስት ሲሆን፣ የቢሾፍቱ ከባህር ጠለል በላይ ያለው ከፍታ አውሮፕላኖች ብዙ ነዳጅና ጭነት እንዲይዙ ስለሚረዳቸው በቀጥታ ወደ ሰሜን አሜሪካ ለሚደረጉ በረራዎች እጅግ አመቺ መሆኑን አያይዞ ገልጿል።

ከሌሎች የባህረ ሰላጤው ሀገራት አየር መንገዶች እንደ ኤሚሬትስ እና ኳታር የሚመጣው ጠንካራ ውድድር ፕሮጀክቱ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ነው ያመላከተው። የቻይናው ሺንዋ በዋናነት የአውሮፕላን ማረፊያውን ከሌሎች መሠረተ ልማቶች ጋር ያለውን ትስስር አጉልቷል።

ከአዲስ አበባ እስከ ቢሾፍቱ የሚዘረጋው በሰዓት እስከ 200 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ 38 ኪሎ ሜትር የፈጣን ባቡር እና ዘመናዊ ባለ ብዙ መስመር አውራ ጎዳና የግንባታው አካል መሆናቸውን ዘግቧል።

ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መሠረት አህጉራዊ ትስስርን እንደሚያጠናክርም ገልጿል። ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ሪቪው የተሰኘው እና የዘርፉ ባለሙያዎች የሚከታተሉት ሚዲያ ስለ አውሮፕላን ማረፊያው ዲዛይንና ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ ዘግቧል። ፕሮጀክቱ “አረንጓዴ” ፕሮጀክት መሆኑንና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጀበ የአውሮፕላን ማረፊያ ከተማ የሚገነባበት መሆኑንም አብራርቷል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ በፈረንጆቹ 2030 ሲጠናቀቅ ብቻ 26 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ገልጿል። ቢዝነስ ኢንሳይደር የተሰኘው መገናኛ ብዙሃን ደግሞ፣ ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን የአቪዬሽን መሪነት እንዴት እንደሚያጠናክርላት ዘግቧል።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑ ባወጣው ዘገባ፣ አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ሲጠናቀቅ በአሁኑ ሰዓት የአፍሪካ ቁጥር አንድ የሆነውን የደቡብ አፍሪካውን ኦር ታምቡ (OR Tambo) አውሮፕላን ማረፊያን በመብለጥ ቀዳሚ እንደሚሆን ገልጿል። ይህም የኢትዮጵያን የ2040 ራዕይ ለማሳካት ቁልፍ መሆኑን አስፍሯል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review