የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ዛሬ ላይ ከደረሰበት የጥበብ ደረጃ ከመድረሱ በፊት፣ ከፅንሰ-ሃሳብ እስከ ምርምር፣ ከመንሳፈፍ እስከ መብረር ድረስ በዘለቀው ፈታኝ ጉዞ አያሌ ውጣ ውረዶች ታልፈዋል።
በዚህ ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ የአካልና የሕይወት መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል። ኢትዮጵያም የዚህ ታሪክ ተካፋይ ብቻ ሳትሆን፣ በአፍሪካ የአቪዬሽን ምስረታ ታሪክ ቀዳሚ በመሆን አሻራዋን ያሳረፈች ሀገር ናት።
ምንም እንኳ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ቢሆንም፣ አየር ኃይል እንደ ተቋም አደረጃጀት ይዞ በይፋ የተመሰረተው ግን ሕዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም ነው። በዚህ ታሪካዊ ቀን ኢትዮጵያዊው ሻለቃ ሚሽካ ባብቼፍ የመጀመሪያው የአየር ኃይል አዛዥ ሆነው ተመደቡ። ከዚያ ቀን ጀምሮ ለዘጠኝ አስርት ዓመታት የዘለቀው የጀግንነት ጉዞ ተጀመረ።
ጀግናው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በ90 ዓመታት የምስረታ ታሪኩ በየዘመናቱ ሁሉ የሀገርን ሉዓላዊነት በመጠበቅ ረገድ የማይተካ ሚና ተጫውቷል።

ተቋሙ የሀገርን የአየር ክልል በጀግንነት ከመጠበቅ ባለፈ፣ በአለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሰማራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ አውለብልቧል። በስልጠናው ዘርፍም ቢሆን የራሱን አባላት ከማብቃት ባለፈ፣ ለሌሎች ወንድም የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል ሙያተኞችን በማሰልጠን የአህጉሪቱ ኩራት መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
በሀገራዊ ለውጡ ማዕቀፍ ውስጥ የተከናወነው ተቋማዊ ሪፎርም አየር ኃይሉን ወደ አዲስ ስልታዊ ምዕራፍ አሸጋግሮታል። “ለታላቅ ሀገር፣ ታላቅ አየር ኃይል” በሚል መሪ ቃል፣ በዘመናዊ ትጥቅ፣ በሰው ኃይል ብቃትና በቴክኖሎጂ የላቀ አየር ኃይል ለመገንባት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
“ታላቅ ተቋም የሚገነባው በታላቅ የሰው ኃይል ነው” በሚል መርህ በእውቀትና በቴክኖሎጂ የሰለጠኑ በርካታ ሙያተኞችን አፍርቷል። ይህም ተቋሙ ዘመናዊ የጥገናና የማሻሻያ ስራዎችን በራስ አቅም ማከናወን እንዲችልና የውጭ ጥገኝነትን እንዲቀንስ አድርጎታል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን “የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና የአንድነት ምልክት” በሚል መሪ ቃል ከጥር 15 ቀን እስከ ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በሚከናወኑ ልዩ ልዩ ኩነቶች በታላቅ ድምቀት ያከብራል።

ይህ በዓል የዘጠኝ አስርት ዓመታት የፈተና እና የድል ጉዞ የሚታይበት፣ የተቋሙ የትናንት ውጣ ውረድ፣ የዛሬ ስኬትና የነገ ተስፋ የሚዘከርበት የታሪክ አውድ ነው።
•በዚህም የተቋሙን የቴክኖሎጂ እድገትና የወደፊት አቅጣጫ የሚያመላክት የአቪዬሽን ኤክስፖ ይካሄዳል ።
• ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ያላትን መሪነትና ወንድማማችነት የምታጠናክርበት የአፍሪካ አየር ኃይሎች ፎረም በኢትዮጵያ አየር ኃይል አዘጋጅነት ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄድ ይሆናል።
• በተጨማሪም በህዝብና በሰራዊቱ መካከል ያለውን የቆየ ትስስር የሚያሳይ እና ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችል ህዝባዊ ውይይትም ይደረጋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለሁለተኛ ጊዜ በሚያዘጋጀው እና ከሌሎች ተጋባዥ የአየር ትርኢት ቡድኖች ጋር በመሆን ሰማዩን በበረራ ጥበብ የሚያደምቁበት የጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት 2026 በልዩ ድምቀት በዚሁ በዓል ላይ ይካሄዳል ።
ይህ በዓል ያለፈውን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በጠንካራውና በዘመናዊው አየር ኃይላቸው እንዲኮሩ ለማድረግ እና ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን የሚጠብቅ ጀግና አየር ኃይል እንዳላት የሚፈታተኗት አካላት እንዲገነዘቡ ለማድረግ እና ወደፊት ተቋሙ የሚገነባውን ግዙፍና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አቅም ለማመላከት ነው።
ዘጠኝ አስርት ዓመታት በሰማይ ላይ፤ ለነፃነትና ለአንድነት የጸና ታሪክ ባለቤት!” – የኢትዮጵያ አየር ኃይል
ከአየር ኃይል ሚዲያ