ኢትዮጵያ ከህንድ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ስራ የባህር በር ፍላጎቷን ለመመለስ የሚረዳ ነው

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከህንድ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ስራ የባህር በር ፍላጎቷን ለመመለስ የሚረዳ ነው

AMN- ጥር 5/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የህንድ ውቂያኖስን ከምትጠቀመው ህንድ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ስራ የባህር በር ፍላጎቷን ለመመለስ እንደሚረዳ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል፡፡

በአንድ ወቅት የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ወደቦቿን አጥታ የበይ ተመልካች ሆና ቆይታለች፡፡

ሀገሪቱ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት የባህር በር ጥያቄን እንዳታነሳ እና አጀንዳው እንዲዳፈን ተደርጎም ቆይቷል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ሀገርና የፈጣን ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ የህዝብ ቁጥሯን የሚመጥን እና ኢኮኖሚዋን የሚሸከም የባህር በር አጥብቃ ትፈልጋለች፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የሀገሪቱ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለቀጣናው ሀገራት የጋራ እድገት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ በስተቀር በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ ሀገራት በሙሉ የባህር በር እንዳላቸው ያነሱት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ጊዜው እድገት የተሳሰረበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

የቀጣናው ሀገራትም የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ለኢትዮጵያም ለእነሱም እድገት መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባቸው እና ክፋት ቀርቶ ትብብር መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በኢጋድ ማዕቀፍ አንድ መሆን እንደሚገባና አሁን ደግሞ የባህር በር አስፈላጊነትን ይበልጥ በሚያጎላው በአፍሪካ ደረጃ በመጣው የነፃ ንግድ ቀጣና ማዕቀፍም መተባበር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር 60 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ ብትሆንም በአንዳንድ አካላት የአግላይነት እንቅስቃሴዎች እንደሚስተዋሉ የጠቆሙት አምባሳደር ዲና፣ መሰል እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የያዘችውን አጀንዳ አሁንም እንዳለቀቀች በማንሳት፣ የቀይ ባህር አካል እስከሆነች ድረስ የቀይ ባህር ካውንስል አባልነት ጥያቄን በየጊዜው እያነሳች መሆኗን ገልጸዋል፡፡

በጋራ የመጠቀም ፍትሃዊ መርህን አንግባ መብቷን እየጠየቀች ያለችው ኢትዮጵያ፣ ፍላጎቷን ለማሳካት በዲፕሎማሲው ረገድ ጠቃሚ ከሆኑ ህንድን ከመሳሰሉት ሀገራት ጋር የተከናወኑ ሥራዎች ለዚህ እንቅስቃሴ ብርቱ ማሳያ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review