በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነዉ የወንዞች ዳርቻ ልማት የ’ይቻላል’ እሳቤን በተግባር የገለጠ ነዉ ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ “በአዲስ አበባ ወንዞች ትንሳዔ” በሚል ርዕስ በተዘጋጀዉ ዘጋቢ ፊልም ላይ በመዲናዋ የተከናወኑ የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን አስመልክቶ በሰጡት ገለጻ ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያውያንን የ”ይቻላል” እሳቤ በተግባር የገለጠ ነዉ ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በከተማዋ የነበሩት ወንዞች እንኳን በጀልባ ሊኬድባቸው፣ ለመዝናኛነትም የማይመቹ እንደነበሩ ያስታወሱት ከንቲባዋ፣ የወንዞቹ ተፈጥሯዊ ይዘት መጥፋትና ይደርስባቸው የነበረው ብክለት ለሰው ልጅ ጤናና ሕይወት አስጊ ሆኖ መቆየቱንም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን እነዚህን ወንዞች ስነ-ምህዳራዊ ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ በማልማት፣ ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻና ጤናማ አካባቢ እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህም አዲስ አበባ እንደ ሌሎች የዓለም ትልልቅ ከተሞች ለመዝናኛነት ብቻ ሳይሆን፣ የቱሪዝም የስበት ማዕከል በመሆን የኢኮኖሚ ምንጭ መሆን እንደምትችል በተግባር የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል።
“ሀገራችን የዓለምን ትኩረት ስባ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የምትችልበት እምቅ ሀብት አላት” ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ እየተገነቡ ያሉት ልማቶች አንዱ ለሌላው ግብዓት በመሆን የተቀናጀ ሀብት መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
“ድህነትን ማውራት ብቻ ችግርን አይፈታም” ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ መፍትሄዎችን በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ለውጥና ብልጽግና እንደሚመጣ አረጋግጠዋል።
ብልጽግና ሊረጋገጥ የሚችለው ዓይናችንን ገልጠን ያሉንን ጸጋዎች ወደ ሀብት በመቀየር ነዉ ብለዋል፡፡
ይህ ፕሮጀክት “ኢትዮጵያውያን አይችሉም፣ እጆቻቸውም ሰርተው የሚያስደንቅ ውጤት አያመጡም” የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት በስራ ለመቀየር የታለመ መሆኑንም ከንቲባዋ አስገንዝበዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ